የሀገር ውስጥ ዜና

ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ከሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጋር ተወያዩ

By Tibebu Kebede

January 24, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥር 15 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ከሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ጋር ተወያዩ።

ፕሬዚዳንቱ በሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ከተመራውን የልዑካን ቡድን ጋር በትናንትናው እለት መወያየታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

በውይይታቸውም ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ፥ በሐረር እና በጂቡቲዋ አርታ ከተሞች መካከል ባለፈው ሳምንት የተደረሰውን የእህትማማችነት ስምምነት አድንቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበችው የሐረር ከተማ በትምህርትና ምርምር ለሚደረጉ ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደምታበረክት ገልጸዋል።

ሐረር እና አርታ ከተሞች በደረሱት የእህትማማችነት ስምምነት መሰረት በመካከላቸው ያለውን እምቅ እድል እና ልምድ በመጠቀም ለኢትዮጵያ እና ጂቡቲ እድገት አስተዋጽኦ ያበረክታሉም ነው ያሉት።

የሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፥ በጅቡቲ ጉብኝታቸው ስለተደረገላቸው መልካም አቀባበልና መስተንግዶ በራሳቸው እና በልዑካን ቡድኑ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ጅቡቲያውያን ሁለተኛ ከተማቸው በሆነችው ሐረር ጉብኝት እንዲያደርጉም ጋብዘዋል።

የሐረር እና የአርታ ከተሞች ግንኙነታቸውን ይበልጥ በማጠናከር በትምህርት እና ምርምር፣ በባህል፣ በንግድ እንዲሁም በግብርና በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ባለፈው ሳምንት መፈራረማቸው ይታወሳል።