አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሂደት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት በሚያስጠብቅ መልኩ መከናወን እንዳለበት ምሁራን ገለጹ፡፡
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል መኮንን ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ምርጫ ሲቃረብ የሚበራከተው የጥላቻ ንግግር ሂደቱን በግጭት እና ፍርሃት የተሞላ ሊያደርገው እንደሚችል ተናግረዋል።
ለዚህም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ዋልታ ረገጥ አካሄዶችን ማረቅ የሚችሉ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪው የፕሮፌሰር ሃብታሙ ወንድሙ፥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የሀገርን ሰላምና ደህንነት በማስቀደም ፕሮግራማቸውን በተገቢው መልኩ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የሚሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጸብ አጫሪ እና ተንኳሽ ቅስቀሳዎች መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
መሰል ድርጊቶች በምርጫው ሂደት ላይ የሚኖራቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ፕሮፌሰሩ፥ ደጋፊዎቻቸው ወዳልተገባ ድርጊት እንዳይገቡም የግንዛቤ መፍጠር ስራ ማከናወን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ደመቀ አጪሶ በበኩላቸው፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥላቻ እና መለያየትን ከሚሰብኩ ቅስቀሳዎች በመቆጠብ ጽንፍ የረገጡ ሃሳቦችን ማስታረቅ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው አውስተዋል።
ፓርቲዎች ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ ፕሮግራሞችንና ፖሊስዎችን በማቅረብ ምርጫው ያለምንም የሰላም ችግር እንዲከናወን የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በምረጫ ቅስቀሳ ሂደት ላይ ለሰላምና ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጡ ይገባል ያሉት ምሁራኑ፥ ሀገራዊ ክብርና አንድነት ሁሉም ፓርቲዎች የማይደራደሩባቸው መስመሮች ሊሆኑ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ፓርቲዎቹ የሚያካሂዱት የምርጫ ቅስቀሳም የምርጫ ቦርድን የጊዜ ሰሌዳ ያከበረ እንዲሁም የምርጫ ህጉን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።
በሃይለኢየሱስ መኮንን