አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በምርጫው እለት በጊዜ በመገኘት ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችና በከተማው የፅዳት ስራ ላይ ተቀጥረው እየሰሩ የሚገኙ የፅዳት ባለሞያዎች ተናገሩ።
ከፋና ጋር ቆይታ ያደረጉ በከተማዋ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች÷ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች የአንድ ሰው ድምፅ ዋጋ እንዳለው አውቀው በምርጫው መሳተፍና ድምፅ መስጠት ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል ።
ደራሲና የህግ ባለሞያ የሆኑት አቶ ዳግማዊ አሰፋ÷ በአካላቸው ላይ በደረሰ ጉዳት አካል ጉዳተኛ የሆኑ ቢሆንም በማንኛውም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፍ እንዳላገዳቸው ይናገራሉ።
ለመንቀሳቀስ የሰዎችን ድጋፍ የምፈልግ ቢሆንም በተቻለኝ አቅም ግን በምርጫ ጣቢያ ተገኝቼ ድምፄን እሰጣለው ብለዋል።
በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አካል ጉዳተኞችም ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ሌላኛዋ አካል ጉዳተኛ ከአስራ ሁለት አመት በፊት ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን የነገሩን ወይዘሮ እመቤት ገ/ኪዳን በሀገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍና ድምፅ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በራሳቸው ተነሳሽነት በምርጫ ጣቢያ በመገኘት የምርጫ ካርዳቸውን እንደወሰዱና በምርጫው እለትም በጊዜ ተገኝተው ድምፅ እንደሚሰጡም ገልጸዋል።
የቤተሰብ መሪዎችን በተመለከተ ለአካል ጉዳተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል ሲሉም መልዕታቸውን አስተላልፏል።
አካል ጉዳተኞች የመምረጥ የመመረጥ መብት እንዳላቸው አውቀው በየትኛውም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸውም ብለዋል።
በከተማው ውስጥ በከተማ የፅዳት ስራ ላይ ተቀጥረው እየሰሩ የሚገኙት ወይዘሮ አይናለም ዻውሎስና ወይዘሮ አማረች ጓሹ የምርጫ ካርድ ወስደው ለመምረጥ እየተዘጋጁ እንደሆነ ተናግረዋል።
በየአካባቢያቸው የሚገኙ ዜጎችም ድምፅ ለመስጠት የምርጫ ካርድ ወስደው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ለጣቢያችኝ ገልፀዋል።
ከሰላም ጋር በተያያዘ ግን ሰላም የሁሉ ነገር መሠረት በመሆኑ የሀገራችንን ሰላም በጋራ ልንጠብቅ ይገባል ብለዋል።
በብርሃኑ በጋሻው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!