አዲስ አበባ፣ ጥር 14፣ 2012 (ኢፍ ቢ ሲ) በዳቮስ እየተካሄደ ባለው የዓለም የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ “ከግለሰብ ያለፈ አካታች ፋይናንስ፣ የጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሚና” በሚል ርዕስ ውይይት ተካሂዷል።
በፎረሙ የፋይናንስ አካታችነትን በተለይም በታዳጊ ሃገራት ለማስፋፋት የተያዘውን ግብ ለማሳካት መካከለኛና አነስተኛ ተቋማት ያላቸውን ሚና በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ መክሯል።
ሃገራት የፋይናንስን አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማስፋፋት በሚችሉባቸው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን እና ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የትግበራ ስልቶች ላይም መድረኩ ምክክር ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መንግስት አካታች የፋይናንስ ስርዓትን በማስፋፋት መካከለኛና አነስተኛ ተቋማት ለመደገፍና ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በመድረኩ ላይ ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግስት ተንቀሳቃሽ የባንክ ወኪሎች አሰራር መመሪያ በማዘጋጀት፣ የብሄራዊ የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ለመፍጠር የሚያስችል ስትራቴጂ በመቀየስና አካታች የፋይናንስ ስትራቴጂውን የመከለስ ተግባር እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።
በውይይቱ የአካታች የፋይናንስ ግቦችን ለማሳካት ተገቢ የሆኑ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብር ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገልጿል።
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኔዘርላንድሷ ንግስት ማክሲማ ኃላፊነትን የተላበሰና የሰዎችን የኑሮ አቅም ያገናዘበ የፋይናንስ አገልግሎት ለሁሉም ሊደርስ ይገባል ብለዋል።
የተመድ አካታች የልማት ፋይናንስ ዋና ጸሀፊ ልዮ መልዕክተኛ የሆኑት ንግስቲቷ ከኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በዳቮስ ተወያይተዋል።
በዘንድሮው የዓለም የኢኮኖሚክ ፎረም የሀገራትና መንግስታት መሪዎችን ጨምሮ ከ3 ሺህ በላይ የባንክ ሀላፊዎች፣ የፋይናንስ ባለሙያዎች እና ባለሃብቶች እየተሳተፉ ይገኛል።