አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 10፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከል ሊገነባ ነው፡፡
የልህቀት ማዕከሉ ከአለም ባንክ በተገኘ ከ24 ሚሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ የሚገነባ መሆኑን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ዶከተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ለማዕከሉ ግንባታ በኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
ማዕከሉ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የሚገነባ ነው ተብሏል፡፡
ግንባታው የስልጠና ተደራሽነትን ማስፋት፣ የትምህርትና ሥልጠና ጥራትን ማሻሻል እንዲሁም ቀጠናዊ ትስስርን ማጠናከርን እንደሚያስችል ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ በብረታ ብረት እንዲሁም ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ላይ ትኩረት ያደርጋልም ነው የተባለው፡፡
በስነስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ወርክሾፖች ጉብኝትና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር መከናወኑን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።