አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እና አህጉር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም የአፍሪካ መሪዎች በአንድ መድረክ የተሰባሰቡበት “የአፍሪካ ሰላም ግንባታ” የፊት ለፊት ውይይት ተካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ ጠንካራ አህጉር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መካከል ሰላማዊ ድባብ እንዲሰፍን እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ መስተጋብር እንዲፈጠር በኢትዮጵያ ያልተቋረጠ ጥረት ተስፋ ሰጭ ውጤት መመዝገቡንም አውስተዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ የሚፈታተኑ ሁኔታዎችን ለመሻገር እና አስተማማኝ ሰላም ለመገንባት ፅኑ ፍላጎት እንዳላትም አረጋግጠዋል።
በመድረኩ የታደሙት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በበኩላቸው፥ የአህጉሪቱን ዘላቂ ሰላም የማረጋገጥ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የማጠናከር አጀንዳ ወቅታዊ ምላሽ እንደሚሻ ገልጸዋል።
አፍሪካ ከሌሎች አህጉራት ጋር ሊኖራት የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር በሚጠበቀው ልክ አለመጠናከሩን ያመላከቱት መሪዎቹ፥ በችግሩ ውስብስብነት ዙሪያ መግባባት ላይ ደርሰዋል።
በመድረኩ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እና በቀጠናው የተረጋጋ ሰላምን ለማምጣት የተደረሰበት ውጤት በመልካም ተሞክሮነት መቅረቡን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በመድረኩ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያን ውጤታማ ተሞክሮ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር መቃኘት እንደሚገባቻው የተነሳ ሲሆን፥ ተጨባጭ አህጉር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በጋራ ለመፍጠር ተስማምተዋል።