አዲስ አበባ፣ ጥር 14 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ በአምስት ክልሎች ለሚተገበረው የማህበረሰብ ንጹህ መጠጥ ውሃ እና የጤና አጠባበቅ (ኮዋሽ) ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ስምምነት ተፈራረሙ።
ከፊንላንድ የመጡ የኮዋሽ ፕሮጀክት ሃላፊዎች፣ የቴክኒክ አማካሪዎች፣ የኢትዮጵያ የኮዋሽ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የኮዋሽ ቡድን መሪ በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ቅንባባ ቀበሌ የሚከናወኑ የፕሮጀክቱን ስራዎች ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያለው ስራ በተቀናጀ እና በተፋጠነ ሁኔታ እየተሠራ መሆኑን የኮዋሽ የቴክኒክ አማካሪና አስተባባሪ አርቱ ሱሚናንት ተናግረዋል።
በዚህ ወቅትም የሃገራቱ የገንዘብ ትብብር ለ4ኛው ዙር የኮዋሽ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ1 ቢሊየን 344 ሚሊየን ብር ስምምነት መፈራረማቸውን አስተባባሪው አንስተዋል።
ከዚህ ውስጥ 644 ሚሊየን ብሩ በፊንላንድ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፥ 700 ሚሊየን ብሩ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ሚሸፈን ይሆናል።
በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የፕሮጀክቱ ተጠቃሚዎች ፕሮጀክቱ ውሃ ፍለጋ ለሰዓታት ያደርጉት የነበረውን ጉዞና እንግልት በማስቀረት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።
የአሁኑ ስምምነቱ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ትግራይ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሚተገበረው የማህበረሰብ ውሃ፣ ንፅህና እና ጤና አጠባበቅ ማስፈጸሚያ የሚውል ይሆናል።
የፊንላንድ እና ኢትዮጵያ የገንዘብና ቴክኒክ ትብብር ባለፉት 25 ዓመታት በአምስቱ ክልሎች በሚገኙ 76 ወረዳዎች፥ በንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ንጽህና እና ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ሲሰራ መቆየቱን አስተባባሪው ጠቅሰዋል።
በዚህም 6 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች በአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን የጠቀሱት አስተባባሪው፥ ለስራው ማስፈጸሚያ ፊንላንድ 2 ነጥብ 8 ቢሊየን እንዲሁም ኢትዮጵያ 700 ሚሊየን ብር ወጪ ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በናትናኤል ጥጋቡ