ቢዝነስ

የኢትዮ-ኮሪያ የቱሪዝም ፎረም በበይነ መረብ ተካሄደ

By Tibebu Kebede

June 11, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 4 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያና በደቡብ ኮሪያ መካከል በኢኮኖሚ መስክ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ‘ኢትዮጵያ-ኮሪያ 2021 የቱሪዝም ፎረም’ በሚል ርዕስ የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር በደም የተሳሰረ ታሪክ እንዳላት ጠቅሰው፥ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መስህቦች፣ ማራኪና ሳቢ ስነ-ምህዳር፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ በርካታ እንስሳትና እጽዋት እንዳሉ እንዲሁም በቂ መሰረተ ልማት፣ የመንግስት ድጋፍና የጎብኚ መዳረሻዎች እንዳሉ አስታውቀዋል።

በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ በበኩላቸው ደቡብ ኮሪያና ኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የፖለቲካ እና ታሪካዊ ትስስር ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ የጉዞ እና የቱሪዝም ምክር ቤት ኢትዮጵያ ተመራጭ የቱሪዝም ስፍራ በማለት የሰጠውን ማረጋገጫ አስታውሰው፥ የኮሮና ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ የደቡብ ኮሪያ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ ጉብኝት እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡

በፎረሙ ስለ ኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ ልዩ ልዩ ፓኬጆች፣ ስለ ማህበራትና አየር መንገዱ አሰራርና ለአስጎብኚ ድርጅቶች ስለሚሰጡ ድጋፎች በተመለከተ ገለጻ ተደርጓል፡፡

በፎረሙም ላይ ከኢትዮጵያ 20 የሚሆኑ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ከደቡብ ኮሪያ 18 አስጎብኚ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!