አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ባለፉት 11 ወራት በደረሰ የትራፊክ አደጋ 119 ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ዲቪዥን ኃላፊ ኢንስፔክተር ቶሎሳ ጎሹ በተለይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስታወቁት በ11 ወራት 149 የትራፊክ አደጋዎች ደርሰዋል፡፡
በደረሱት አደጋዎች የ119 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ22 ሰዎች ላይ ከባድ፣ በስምንት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ባለፈም ከ14 ሚሊየን ብር በላይ የንብረት ውድመት መድረሱን እና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የአደጋዎቹ ቁጥር ከፍ ማለቱንም ነው የተናገሩት፡፡
በአካባቢው ያለው የመሬት አቀማመጥ ወጣ ገባ የሚበዛበት መሆን፣ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ የተለያዩ አደንዛዥ እፆችን እየተጠቀሙ ማሽከርከርና ያለመንጃ ፍቃድና እድሜያቸው የማይፈቅድላቸው ህፃናት ማሽከርከር ለአደጋዎቹ መንስኤ እንደሆኑም ገልጸዋል፡፡
ከደረሰው አደጋ በተያያዘ በተያያዘ 149ኙም ጉዳዮች በፍርድ ቤት እየታዩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አስራ ዘጠኙ ውሳኔ ሲያገኙ 101 በምርመራ እና የተቀሩት በቀጠሮ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በተሾመ ኃይሉ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን