Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል የእናቶችና ህጻናት ህክምና ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል የእናቶችና ህጻናት ህክምና ማዕከል ተመርቆ ተከፈተ፡፡

የጤና ሚኒስት ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ማዕከሉን መርቀው ከፍተዋል።

ማዕከሉ ባለሶስት ፎቅና ከሶስት መቶ በላይ ክፍሎች ያሉት ሲሆን የግንባታው ወጪም 60 ሚሊዮን ብር መሆኑ ተገልጿል።

እንደሀገር ትልቅ ትኩረት የሚሰጠውን የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል ዶክተር ሊያ ታደሰ።

ለማዕከሉ እንደ ጤና ሚኒስቴር የቅርብ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ጠቁመው ይህን ተግባር የፈፀሙ አካላትን አመስግነዋል።

በተያያዘ ዜና “ኑ ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል ሶስተኛው ዙር ሀገራዊ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ዛሬ ተካሂዷል።

ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ በደቡብ ክልል የሚገኙ የዘጠኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች የተሳተፉበት ሲሆን ከ500 ሺህ በላይ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል።

በማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶን ጨምሮ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ተሳትፈዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ከ500 ሺህ በላይ ለመብል የሚሆኑ እንዲሁም አካባቢ መጠበቅ የሚችሉ ችግኞች መዘጋጀቱን ገልፀው ከመትከል ባሻገር ችግኞች ፀድቀው አካባቢን እስከሚቀይሩ ድረስ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው አውስተዋል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ይርዳው “በሀገራችን አዲስ ታሪክ እየተፃፈበት የሚገኘውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለማሳካት ዩኒቨርሲቲው እየሰራ ላለው አስተዋጽኦ አመስግነው፥ ከተከላው ባሻገር አካባቢውን ለመጥቀም የሚችሉ ችግኞችን ለይቶ መትከሉን እንደ ሞዴል መውሰድ አለብን” ብለዋል።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት ሁለት አመታት በተካሄዱ ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮች ላይ ከ150 ሺህ በላይ ችግኞች ተተክለው መፅደቅ ችለዋል።

በመለሰ ታደለ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version