አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋሲል ማእድ የንጉስ እራት በሚል ክለቡን በገቢ ለማጠናከር ያለመ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር በአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ቅጥር ግቢ ዛሬ ምሽቱን ተካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልላዊ መንግስትርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ÷ ለፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ርእሰ መስተዳድሩ በአማራ ክልል ታሪክ በእግር ኳስ ስፖርት ዘርፍ እየታየ ያለው መሻሻል ዘርፉን ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ተስፋን የሰነቀ ነው ብለዋል።
“ፋሲል ከነማ ባለፉት አመታት ባደረገው ብርቱ ስፖርታዊ ጥረት ታሪክ የቀየረ የአሸናፊነት ድል ማስመዝገብ በመቻሉ ለክልሉ ህዝብ ኩራት መሆን ችሏል” ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሰት ክለቡን በበጀት ከመደገፍ ጀምሮ የስፖርት ዘርፉን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመው ለክለቡ ገቢ መጠናከር የገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ የክልል መንግስታትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ከንቲባና የፋሲል ከነማ የእግር ኳስ ክለብ ፕሬዘዳንት አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው÷ “የክለቡ አሸናፊነት የጎንደርን ታሪክ ያደሰ ታላቅ ስፖርታዊ ክንዋኔ ነው”ብለዋል፡፡
ክለቡ ጠንካራ ወንድማማችነትና አንድነትን በማጎናጸፍ ስፖርት ለወዳጀነትና ለፍቅር የሚለውን መርህ በተግባር ያስመሰከረ የልፋትና የድካም ውጤት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ክለቡን በገቢ ለማጠናከር ሰፊ ራእይ በመያዝ ወደ እንቅስቃሴ ገብቷል ያሉት ከንቲባው÷ በጎንደር በባህርዳርና በአዲስ አበባ ለገቢ ማስገኛ የሚውሉ የገበያ ሞሎችንና የንግድ ተቋማትን ለማቋቋም መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡
ለክለቡ ማጠናከሪያ በአዲስ አበባ በባህርዳርና ዛሬ ምሽት ደግሞ በጎንደር በተካሄዱ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ከ200 ሚሊየን ብር በላይ ቃል መገባቱንም ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
በፋሲል አብያተ መንግስት እየተካሄደ ባለው የክለቡ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የክለቡ ተጫዋቾችና አመራሮች፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የከተማው አመራሮች ተሳታፊ መሆናቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!