አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የጎጎታ ኬር የከንባታ ጠምባሮ ዞን ህዝብ የልማት ማህበር 25ኛ ዓመት የእዮቤልዩ የማጠቃለያ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል።
በኮንፈረንሱ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፍቃዱ፣ የከንባታ ጠምባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ መለሰ አጨሶ ፣ ሚኒስትሮች ፣ የፌደራል እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የዞኑ ተወላጆች በተገኙበት በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በኮንፈረንሱ፥ ኢትዮጵያ የምትደምቀው ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች በአንድነት እና በፍቅር ተባብረው ሲኖሩ ነው ብለዋል።
አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ባህላቸውን እና ማንነታቸውን የሚያንጸባርቁባት ከተማ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ አዳነች፥ በቅርቡም የኢትዮጵያ ባህል ማዕከል በከተማዋ ለማደራጀት ዝግጅት መጀመሩን ገልጸዋል።
የከንባታ ጠምባሮ ዞን ህዝብም ባህሉን ፣ታሪኩን እና እሴቱን ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን እና ለአለም የሚያስተዋውቅበት የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ መስጠቱን ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በኮንፈረንሱ ተናግረዋል።
የልማት ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮባለፉት 25 ዓመታት የከንባታ ጠምባሮ ዞንን እና አካባቢውን ማህበረሰብ በተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ ማድረጉን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የከንባታ ጠምባሮ ዞን ህዝብ ባህሉን ፣ታሪኩን እና እሴቱን እንዲያንጸባርቅ የባህል ማዕከል መገንቢያ ቦታ በመስጠቱ በዞኑ ህዝብ ስም አመስግነዋል።
በዕለቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በኢትዮጵያ እና ለዞኑ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የእውቅና ሽልማት መበርከቱን ከአዲስ አበባ ከተማ ፐረስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!