Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቪዛ ክልከላው የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የፖሊሲ ነጻነት የመንሳት ምልክት ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የስራ ኃላፊዎች ላይ የጣለው የቪዛ ክልከላ የሁለቱን ሃገራት የ120 አመታት ግንኙነት ቁመና የማይመጥን መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም ውሳኔው ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዜሮ የሚያባዛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቪዛ ክልከላው በየትኞቹ የኢትዮጵያ መንግሥት የስራ ኃላፊዎች ላይ እንደተላለፈ እስካሁን ዝርዝር ነገር የለም ያሉት ቃል-አቀባዩ፥ ዕገዳው ኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለውጫና ባይጠፋም አሜሪካንም ሆነ የአፍሪካ ቀጠናን ተጎጂ የሚያደርግ እና ዕገዳውን ለመጣልም በቂ ምክንያት የሌለ በመሆኑ ተቀባይነት አይኖረውም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከሰብአዊ መብት አያያዝ ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መታዘብ የቻሉት ማሻሻያ ማድረጉ እየታወቀ እንዲህ አይነት እርምጃ ለመውሰድ መነሳት የሃገሪቱን እና የአፍሪካን የፖሊሲ ነጻነት የመንሳት ምልክት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከጉልበት እና ሃብት ጋር በማያደራድር እና የሃገራቱንም የግንኙነት መንፈስ በማያጋግል መንገድ ነገሮችን ትመለከታለችም ነው ያሉት፡፡

ዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ” በትግራይ ክልል ከተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ የኬሚካል የጦር መሳሪያ በዜጎቿ ላይ ተጠቅማለች” በሚል ያሰራጩት ዘገባ ከእውነት የራቀ እንደሆነ ቃል-አቀባዩ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

የሱዳን እና ግብፅ ጥምር ጦር ከሰሞኑ የጋራ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን በተመለከተም ሃገራቱ በጋራ ያሻቸውን ነገር ማከናወን የሚችሉ ሲሆን በኢትዮጵያ ኪሳራ እና ሉዓላዊነት ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን ግን በንቃት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩልም 24 ሰዓት የሚሰራ መከላከያ እንዳለን ሊታወቅ ይገባልም ብለዋል ቃል-አቀባዩ በሰጡት መግለጫ፡፡

በሶዶ ለማ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version