Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የቆላ አጋዘን የገደለ 100 ከብት ወይም ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል አባ ገዳዎች ወሰኑ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአብጃታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ ህልውናው አደጋ ላይ የወደቀውን የቆላ አጋዘን የገደለ ሰው 100 ከብት ወይም ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል የአርሲ ነገሌ ወረዳ የዳዌ ደቦ አብዩ ጎሳ አባገዳዎች ውሳኔ አሳለፉ።

ውሳኔው የቆላ አጋዘን የመጥፋት አደጋ ስጋቱን እንደሚቀንስ ተመላክቷል።

አባ ገዳ ቱፋ ዳራርሶ በወቅቱ እንደገለፁት÷ በሲቄ ተራራ የሚገኘው የቆላ አጋዘን በአካባቢው ማህበረሰብ ጉዳት እየደረሰበት ለመጥፋት ተቃርቧል።

የዳዌ፣ ደቦና አብዩ ጎሳ አጋዘኑን በገዳ ስርዓት እንደ አብራክ ልጃቸው እንዲያዩ፣ የሰው ልጅ ያለውን ክብርና እንክብካቤ እንዲያገኝ በገዳ ስርዓት በሞጋሳ የራሱ ማድረጉን ተናግረዋል።

የጎሳው ማህበረሰብ አጋዘኑን እንደ ራሱ ልጅ በማየት ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ ያደርጋል ያሉት አባገዳው÷ በዚህም አጋዘኑን የገደለ “የሰው ህይወት እንዳጠፋ ይቆጠራል  ብለዋል።

በመሆኑም የቆላ አጋዘን የገደለ ሰው የሚጣልበት ቅጣት ወይም የሚከፍለው ካሳ በሰው ህይወት ልክ የሚወሰን እንደሚሆን አመልክተዋል።

ህብረተሰቡ በአርሲ ነገሌ ወረዳ አብጃታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ያለውን አጋዘን እንዳይነካ ከማድረግ ባለፈ ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ ያደርጋል ሲሉም ተናግረዋል።

“በአባ ገዳ ውሳኔ መሰረት አጋዘኑን የገደለ ሰው በ100 ከብት ይቀጣል፤ ወይም ተመጣጣኝ ካሳ/ጉማ ይከፍላል” ተብሏል።

ማህበረሰቡም አካባቢው በደን እንዲሸፈን፣ መጠለያና መኖሪያ አካባቢውን በማልማት የድርሻውን ለመወጣት መወሰኑን አስታውቀዋል።

የአብጃታ ሻላ ብሔራዊ ፓርክ ሃላፊ አቶ ሚኤሶ ሀብኖ እንደገለፁት÷ ውሳኔው በሲቄ ተራራ ያለው የቆላ አጋዘን እንዳይጠፋ ህብረተሰቡ ሀብቱን ከጥፋት ለመታደግና የመኖር ህልውናው እንዲለመልም የሚያስችል ነው።

በተለይም የተራቆተው ደን እንዲመለስና አጋዘኖችን ጨምሮ የዱር እንስሳት መጠለያ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው÷ የኦሮሞ ህዝብ መሰረት የሆነው የገዳ ስርዓት እንስሳት ለሰው የሚሰጠውን መብት እንዲያገኙ ያስቻለ አኩሪ ህግና ስርዓት ነው ብለዋል።

አቶ ኩመራ አክለውም በሰንቀሌ ብሔራዊ ፓርክ በሀምቤንቱ ጎሳ ከዚህ ቀደም የተላለፈ የገዳ ስርዓት ህግና መመሪያ ውሳኔ ቁጥራቸው ከ70 በታች ወርዶ ለመጥፋት የተቃረቡ ቆርኬዎችን ለመታደግ ያስቻለ መሆኑን አስታውሰዋል ።

አሁን ላይ በፓርኩ የቆርኬዎች ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ መድረሱን አመልክተዋል።

በሰንቀሌ የተጀመረው በጎ ጅምርና ተሞክሮ ከአብጃታና ሻላ ብሔራዊ ፓርክ ባለፈ በክልሉ ሁሉም የዱር እንስሳት ጥበቃ ፓርኮች መስፋፋት እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡ የተላለፈውን ውሳኔ ወደ ተግባር በመቀየር በሰንቀሌ ያየነውን ውጤት በአጭር ጊዜ ማየት እንድንችል ሊያደርግ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በስነ ስርዓቱ ላይ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ህብረተሰብ ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version