Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በዳርፉር የተፈፀመውን የጦር ወንጀልና የሰብዓዊት መብት ጥሰት የሚመለከት ልዩ ፍርድ ቤት ሊመሰረት ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ (ኤፍ ቢ ሲ) የሱዳን መንግስት እና የዳርፉር ታጣቂ ቡድኖች  የዳርፉርን የጦር ወንጀል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚመለከት ልዩ የወንጀል ፍርድ ቤት ለመመስረት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ፡፡

የሱዳን መንግስት እና የዳርፉር ታጣቂ ቡድኖች የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚያደርጉት ሂደት ወደ ጸጥታ ዝግጅቶች ከማምራታቸው በፊት የፓለቲካ ጉዳዮች ላይ በጁባ ውይይት አድርገዋል፡፡

በዚህ ውይይትም የመንግስትና የታጣቂ ቡድኑ ተወካዮች የፍትህ ስርዓቱን በማሻጋገር ላይ እና በእርቅ በኩል ውጤት መመዝገቡን የሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር ህብረት (ኤስ ኤል ኤፍ ኤ) ተደራዳሪ እና የሱዳን አብዮት ግንባር(ኤስ አር ኤፍ) ተደራዳሪ ኢብራሂም ዛሪባ  ተናግረዋል፡፡

በዳርፉር የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የጦር ወንጀል የሚመረምር እና ክስ የሚመሰርት ልዩ የጦር ፍርድ ቤት መመስረትን ጨምሮ ለፍትህ ስርዓቱ እና ለተጠያቂነት አካሄዶችን ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል፡፡

የሱዳን ፍትህ እና እኩልነት ንቅናቄ ተደራዳሪ  አህመድ ቱጉድ በበኩላቸው በዚህ ድርድር በኦማር ሀሰን አልበሽር ዘመን በነበረው የህፃናት ውትድርና ፣ አስገድዶ መድፈር እና በጦር አዛዦች ለፈፀሙት ጥፋት ተጠያቂ አለመሆን በተመለከተ ውይይት እንደተደረገ ገልፀዋል፡፡

ተደራዳሪው ሁሉም ወገኖች  በዳርፉር ምቹ ሁኔታን እና መረጋጋትን ለመፍጠር በሚስችሉ ዝግጅቶች ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን  ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡- ሱዳንት ትሪቡን

Exit mobile version