Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ቦርዱ በመጪዎቹ ቀናት 106 ሺህ 345 ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ እንደሚያሰለጥን ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የተለያዩ ዝግጅቶቸን ሲያከናውን መቆየቱን እና እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።

ግንቦት 7 ቀን 2013 ቦርዱ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር የድምፅ መስጫ ቀን በታቀደለት ግንቦት 28 እና ሰኔ 5 ቀን 2013 መከናወን እንደማይችል በተጨማሪ ከ2 እስከ 3 ሳምንት ዝግጅት ጊዜ እንደሚያስፈልግ መግለፁን አስታውሷል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከሚገኙት 138 ሺህ 655 የምርጫ አስፈጻሚዎች በተጨማሪ በመጪዎቹ ቀናት 106 ሺህ 345 ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ እንደሚያሰለጥን የገለፀው ቦርዱ ከእነዚህ መካከል በቦርዱ መጠባበቂያ ዝርዝር ላይ ተጨማሪ 100 ሺህ 333 አስፈጻሚዎች አሉ ብሏል።

ከእነዚህ ተጨማሪ ምርጫ አስፈጻሚዎች በቦርዱ በተጠባባቂነት የተያዙ ሲሆን ቦርዱ መስፈርቱን የማጣራት እና የማሰልጠን ስራ አጠናቆ ለድምጽ መስጫ ቀን ዝግጁ ያደርጋል ተብሏል።

እንዲሁም ከፍተኛ የአስፈጻሚ ቁጥር ክፍተት ባለባቸው ክልሎች በልዩ ሁኔታ ለመሙላት ጥረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

ለስልጠና ቁሳቁስ እሸጋ እና ስርጭት በአጠቃላይ አራት ቀናት ይፈጃል ያለው ቦርዱ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ከ10 ቀናት በኋላ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ የድምጽ መስጫ ወረቀት፣ ፎርሞች እና ከሌሎች ተገዝተው የተቀመጡ የድምፅ መስጫ ቀን ቁሳቁሶችን በምርጫ ክልል አከፋፍሎ ማሸግ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ከተጠናቀቀ በኋላ አራት ሳምንታት እንደሚፈጅ ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ ቦርዱ የትራንስፓርት እቅድ ያዘጋጀ ሲሆን ከመራጮች ምዝገባ ልምድ በመነሳት የፌዴራል ተቋማት፣ የክልል መንግስታት እና የሌሎች አካላት ከፍተኛ ትብብር ይጠይቃል ነው የተባለው።

ይህ የኦፕሬሽን ዝግጅትም ቦርዱ በሙሉ ሃይሉ አሟጦ በመጠቀም የሚከናወን መሆኑን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚካሄደው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ነው።

ነገር ግን ድምጽ መስጠት ሂደቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከናወንባቸው የማይችልባቸው የምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢዎች እንደሚገኙ ነው ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያመለከተው

በእነዚህ አካባዎች ድምጽ መስጠት ሂደቱ የማይከናወንባቸው ምክንያቶች በጸጥታ ችግሮች የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ቦታዎች ፣ የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ የተቋረጠባቸው ቦታዎች  እና  የመራጮች ምዝገባ ላይ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው ወይም ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ ጉልህ የአሰራር ችግር በማየቱ ማጣራት የወሰነባቸው ቦታዎች ናቸው።

በተለያዩ ምክንያቶች (በጸጥታ እና በመራጮች ምዝገባ አቤቱታ) ድምጽ መስጠት ሂደቱ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተግባራዊ ሊሆን የማይችልባቸው የምርጫ ክልሎችን ቦርዱ የለየ ሲሆን እነሱም የሚከተሉት የምርጫ ክልሎች ናቸው።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል (4 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመባቸው ቦታዎች

  1. መተከል ምርጫ ክልል
  2. ሺናሻ ልዩ ምርጫ ክልል
  3. ካማሽ ምርጫ ክልል
  4. ዳለቲ ምርጫ ክልል

ሶማሌ ክልል (14 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው እና የማጣራት ሂደቱ ላይ የሚወሰኑ

  1. አራቢ የምርጫ ክልል
  2. ደግሃመዶ ምርጫ ክልል
  3. ጎዴ የምርጫ ክልል
  4. ጂግጂጋ 1 የምርጫ ክልል
  5. ጂግጂጋ 2 የምርጫ ክልል
  6. ቀብሪደሃር ምርጫ ክልል
  7. ቀላፎ ምርጫ ክልል
  8. ዋርዴር ምርጫ ክልል
  9. ፊቅ ምርጫ ክልል
  10. ገላዲን ምርጫ ክልል
  11. ደገሃቡር ምርጫ ክልል

የመራጮች ምዝገባ ሂደት በክልሉ መስተዳድር የተቋረጠባቸው

  1. አይሻ ምርጫ ክልል
  2. ኤረር ምርጫ ክልል
  3. ሽንሌ ምርጫ ክልል

ኦሮሚያ ክልል ( 7 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ( በጸጥታ ችግር)

  1. ቤጊ ምርጫ ክልል – ምእራብ ወለጋ
  2. ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል – ምእራብ ወለጋ
  3. አያና ምርጫ ክልል – ምስራቅ ወለጋ
  4. ገሊላ ምርጫ – ምስራቅ ወለጋ
  5. አሊቦ ምርጫ ክልል -ሆሮ ጉድሩ
  6. ጊዳም ምርጫ ክልል- ሆሮ ጉድሩ
  7. ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል- ሆሮ ጉድሩ

አማራ ክልል (8 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው (በጸጥታ ችግር)

  1. ማጀቴ (ማኮይ) ምርጫ ክልል
  2. አርጎባ ልዩ ምርጫ ክልል
  3. ሸዋሮቢት ምርጫ ክልል
  4. ኤፌሶን ምርጫ ክልል
  5. ጭልጋ 1 ምርጫ ክልል
  6. ጭልጋ 2 ምርጫ ክልል
  7. ላይ አርማጭሆ ምርጫ ክልል
  8. ድልይብዛ ምርጫ ክልል

ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል  (4 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው (በጸጥታ ችግር)

  1. ዘልማም ምርጫ ክልል
  2. ሱርማ ልዩ ምርጫ ክልል
  3. ዲዚ ልዩ ምርጫ ክልል
  4. ሙርሲ ልዩ ምርጫ ክልል

ሐረሪ ክልል  (3 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ከፍተኛ የተዛባ አሰራር የታየባቸው እንዲሁም በህግ የተያዘ ጉዳይ

  1. ጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል
  2. ጀጎል መደበኛ ምርጫ ክልል
  3. ጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ ምርጫ ክልል

ልዩ መግለጫ  ሲል ቦርዱ ያስቀመጠው ደግሞ በጋምቤላ ክልል ዲማ ምርጫ ክልል እና አኮቦ ምርጫ ክልል ከፍተኛ የመሰረተ ልማት እና የመጓጓዥ ችግር ከፍተኛ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ የክልል እና የፌደራል መንግስትን ከፍተኛ እገዛ እንደሚጠይቅ ተነግሯል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

Exit mobile version