የሀገር ውስጥ ዜና

በመዲናዋ የኮቪድ19 ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

By Meseret Awoke

May 21, 2021

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)በአዲስ አበባ ከተማ ከትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በተላለፉ ከ1ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ከትራንስፖርት ባለስልጣንና ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ባገኘው ሪፖርት መሰረት ከግንቦት 2 እስከ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ብቻ ትርፍ በመጫን፣ ማስክ አለማድረግ፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ መስመር አለመሸፈን፣ ታፔላ አለመስቀል እና በስራ ሰዓት መቆም በድምሩ 1 ሺህ 2 አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ተብሏል፡፡

ትርፍ በመጫን መተላለፍ፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ የኮቪድ 19 መከላከያ ተግባራት አለማከናወን፣ በስራ ሰዓት ያለ ሥራ ቆሞ መገኘት እና ታፔላ ሳይሰቅሉ መስራት ከ5 መቶ እስከ 2 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ በመመሪያው ተደንግጓል፡፡

መመሪያው ከወጣበት ከሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የንቅናቄ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በዋና ዋና ተርሚናሎች እና መስመሮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

በሚያዝያና መጋቢት ወር 10 ሺህ 305 አሽከርካሪዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን በእነዚሁ ጥፋተኞች ላይ በተወሰደ እርምጃም 4 ሚሊየን 609 ሺህ ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ከትራንስፖርት ቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!