አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)መሠረቱን በአሜሪካ ያደረገው የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚካሄደውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አወገዘ።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡ ወይም አንድ ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት በውጤቱ ላይ ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚሞክሩ ሁሉም የውጭ ኃይሎችን እንደሚያወግዝ ነው ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በላከው ደብዳቤ የገለጸው።
ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት የዴሞክራሲ ምሰሶዎች አንዱ የሆነውን ግልጽ ምርጫ ለማካሄድ ገለልተኛ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ማቋቋም መሆኑን አውስቷል።
ይህም ለዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ሽግግር አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን ነው ያመለከተው።
“የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ ጉዳዮች የሰጠውን ትኩረት እያደነቅን በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ጣልቃ ገብነት ግን የሚያስከተለው አደጋ ያሳስበናል” ያለው የምክር ቤቱ፤ በኢትዮጵያ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ተፈጸመን ጥቃት ተከትሎ እንደሆነ አስገንዝቧል።
የትኛውም ሉዐላዊ አገር እንዲህ አይነት ክህደት ሲፈጸምበት ሊወስደው የሚችለውን እርምጃ የኢትዮጵያ መንግስት መውሰዱን በማመልከት፤ “የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት ሊደገፍ ይገባል” ብሏል።
“ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ከኢትዮጵያ ጋር የምትሰራው አሜሪካ ኢትዮጵያንና ቀጠናውን ለማተራመስ የሚሰራውን የህውሓት የሽብር ቡድን ደጋፊዎችና የውጭ ተባባሪ ድርጅቶችን መከታተል ይኖርባታል” ሲል ማስገንዘቡን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
“አሜሪካ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ፣ ለሁለተኛው ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ድጋፍ እንደምትሰጥና በኢትዮ-ሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ በውይይት እንዲፈታ እንዲሁም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚካሄደው የመልሶ ግንባታና የሰብአዊ ድጋፍን በማገዝ አሜሪካ ገንቢ ሚና እንደምትጫወት እምነታችን ነው” ብሏል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!