አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አዋሽ ባንክ ለተለያዩ ተቋማት 17 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነት ግዴታውን ለመወጣት በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባዘጋጀው የድጋፍ መርሐ ግብር ነው ልዩ ትኩረት ለሚሹ ድርጅቶችና ተቋማት የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው፡፡
በዚህ መሰረት ለኢትዮጵያ ማየትና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር 700 ሺህ ብር፣ ለዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ፋውንዴሽን 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር፣ ለኤስ ኤን ቪ ኔዘርላንድስ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን 2 ሚሊየን ብር፣ ለኬር ኢትዮጵያ 2 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ከዚህ ባለፈም ለሴንትሮ አሉቶ ፐር ኢትዮጵያ 2 ሚሊየን ብር እንዲሁም ለዲቦራ ፋውንዴሽን 10 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ባንኩ ከዚህ ቀደም በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ለዕለት ደራሽ ዕርዳታና መልሶ ማቋቋም፣ በጣና ሐይቅ ላይ ለተከሰተው እምቦጭ አረም ማስወገድና መሰል ተግባር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም በቅርቡ በመንግስት ተቀርፀው ተግባራዊ ለተደረጉና በመደረግ ላይ ላሉት ለሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት 15 ሚሊየን ብር፣ የጎርጎራ፣ ኮይሻ እና ወንጪ ፕሮጀክቶች 30 ሚሊየን ብር፣ ለብሔራዊ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ኮሚቴ 10 ሚሊየን ብር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ማሟያ 3 ሚሊየን እንዲሁም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የ25 ሚሊየን የቦንድ ግዥ መፈፀሙ ይታወሳል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!