አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በለንደን እየተካሄደ ከሚገኘው የብሪታኒያ -አፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ጎን ለጎን ነው ከጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጋር ተገናኝተው የተወያዩት።
በሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ ባተኮረው ውይይታቸውም የኢትዮጵያ እና የብሪታንያ ግንኙነት ወደ ላቀ የትብብር ከፍታ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ ተስማምተዋል።
በተመሳሳይ በቤኪንግሃም ቤተመንግስት በተደረገው የእራት ግብዣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ከልዑል ዊልያም ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ልዑል ዊልያም ኢትዮጵያውያን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁላቸው ሲሆን፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ልዑሉ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ግብዣ አቅርበውላቸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው እለትም ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሻርማ ጋር መወያየታቸውም ይታወሳል።
ውይይታቸው በመሰረተ ልማት፣ በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ያተኮረ መሆኑን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ የሁለቱ ሃገራት የልማት ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሻርማ በበኩላቸው፥ ሃገራቸው ኢትዮጵያ ለጀመረችው የለውጥ ማሻሻያ ተግባር ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
በተያያዘም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዲያጆ ማኔጅመንት ግሩፕ ጋር በኩባንያው እንቅስቃሴ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
ዲያጆ ኩባንያ በሃገሪቱ ከፍተኛ የግብር ከፋይ መሆኑን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በቀጣይ ለኩባንያው ውጤታማ እንቅስቃሴ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በእንግሊዝ የአፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
ውይይቱም ከጉባኤው ጎን ለጎን የተደረገ ነው።