አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)- በትግራይ ህዝብን ማእከል ያደረገ የተረጋጋ ህዝባዊ ሰላምና አስተዳደርን ለማረጋገጥ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ጥሪ አቀረቡ።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በጥሪያቸው “በህዝቦች ዘላቂ ትበብርና በሰላምና መረጋጋት የመኖር ፍላጎት ላይ የጋረጠውን ጉልህ አደጋ በተመለከተ በግልፅ በመተማመን ተገቢውን ፍትህ መስጠት ይፈልጋል” ብለዋል።
ዶክተር አብርሃም ለፋብኮ በላኩት መግለጫ ባስተላፉት መልዕክት ፤ በአገራችን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ጀምሮ በተከሰተው ግጭት መነሻነት በተፈጠሩት መጠነ ሰፊ ጉዳቶች በወገኖች ላይ የደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ መፈናቀሎች፣ ጥልቅ የስነ ልቡና ጉዳቶች፣ የንብረት ዘረፋ መጥፋት፣ ዘረፋና ውድመት፣ አላስፈላጊ መገፋፋትና የተካረሩ አመለካከቶች በአጠቃላይም ውጥረት በህዝቦች ዘላቂ ትበብርና በሰላምና መረጋጋት የመኖር ፍላጎት ላይ የጋረጠውን ጉልህ አደጋ በተመለከተ በግልፅ በመተማመን ተገቢውን ፍትህ መስጠት ይፈልጋል” ብለዋል።
ዶክተር አብርሃም በላይ በርሀ የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግስት ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ በትግራይ ህዝብን ማእከል ያደረገ የተረጋጋ ህዝባዊ ሰላምና አስተዳደርን ለማረጋገጥ ያቀረቡት ጥሪ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በማስቀደም በአገራችን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ከጥቅምት 24 ጀምሮ በተከሰተው ግጭት መነሻነት በተፈጠሩት መጠነ ሰፊ ጉዳቶች በወገኖች ላይ የደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳተኝነት ፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፣ መፈናቀሎች ፣ ጥልቅ የስነ ልቡና ጉዳቶች ፣ የንብረት ዘረፋ መጥፋትና ውድመት፣ አላስፈላጊ መገፋፋትና የተካረሩ አመለካከቶች በአጠቃላይም ውጥረት በህዝቦች ዘላቂ ትበብርና በሰላምና መረጋጋት የመኖር ፍላጎት ላይ የጋረጠውን ጉልህ አደጋ በተመለከተ በግልፅ በመተማመን ተገቢውን ፍትህ መስጠት ይፈልጋል።
የሚደርሰው ጉዳትና ቁስልን በመቀነስና በመሻር እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በተግባር በመቀየር በይቅርታ መንፈስና የቁርጠኛ የሰላም ወዳድነት ማረጋገጫ እርምጃዎችን በመውሰድ አገሬንና ህዝቦችዋን እንዳገለግል በተሰጠኝ በዚህ ትልቅ ሀላፊነት ተመድቤ ስራዬን ስጀምር በክልሉ ህዝብ ፣ በፌደራል መንግስት፣ በመላው የአገራችን ህዝቦች ፣ በዲያስፖራ ኮሚዮኒቲው እና በአለም አቀፋ ማህበረሰብም ጭምር ለዚህ ወሳኝ ተልእኮዬ ስኬት ሙሉ ድጋፍና እገዛ እንደማገኝ ከወዲሁ በሙሉ ልብ በመተማመን ነው።
በትግራይ ክልል ያለው ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ በተለይም ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና መፍትሔን በመፈለግ ሒደት የችግሮችን ስሪተ ነገር የመረዳት ፣የተያያዥ መሰረታዊ ጉዳዮችን ተፅእኖ መለየትና ከሙሉ ስእል እይታ ያልጎደሉ ደረጃ በደረጃ የሚተገበሩ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማፍለቅና በህዝባዊ ይሁንታ በርብርብና በድፍረት በተግባር የመፈፀም ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ባለፋት ወራቶች በትግራይ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ለመቀየር በተሰሩ በርካታ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ጉልህ ተግዳሮቶች የመኖራቸው እውነታ ለፖለቲካ ትክክለኝነት የማይመቹ ከመሆናቸውም በላይ ቅድሚያ ለሚሰጠው የሰው ልጆች ህይወት ማዳን ሰብአዊ ቀውስ እንዳይባባስ የመስራት አንገብጋቢ ጉዳይና በአካባቢው የተሻለ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋትን የማረጋገጥ ስራውን ፈታኝ በማድረግ ለተጨማሪ የከፋ ጉዳት የሚዳርጉ ጉልህ ችግሮች መሆናቸውን መገንዘብም አስፈላጊ
ነገር ነው።
በህግ ማስከበር ዘመቻ ምእራፍና አንዳንድ ግጭትና ጥቃቶች በንፁሀን ዜጎችና በግፊትና በቆሞ ሞት እምቢተኝነት በርካታ ወጣቶች ሴቶች እድሚያቸው ያልደረሱ ታዳጊዎች ጭምር የሞት የአካል ጉዳት አደጋና የንብረት ውድመትም ጭምር የተጋለጡበትን ሁኔታ መቀየር አስፈላጊና አንገብጋቢ ወቅቱ የሚጠይቀው የአመራር እርምጃ ነው።
እዚህ ላይ በፌደራል መንግስት በህግ የማስከበር ምእራፋ የተወሰዱት ጉልህ እርምጃዎች የመንግስትን ህጋዊ ሀላፊነትና ግዴታዎች ለመወጣት የተፈፀሙና በሰላምና ፀጥታ ሀይላት የተሰሩ ስራዎችም በአገር አንድነት እና ሰላም ላይ የተቃጡ አደጋዎችን ለመቀልበስ አስፈላጊነታቸው ታምኖባቸው የተፈፀሙ ግዳጆች ናቸው ።
በዚህም ምክንያት በክልሉ በአሁኑ ወቅት የተገኘውን አንፃራዊ መረጋጋት በማረጋገጥ ረገድ የውድ ህይወት የመስዋእትነት ዋጋ ጭምር የተከፈለባቸው እና አየተከፈለባቸው የተረጋገገጡ መሆናቸውን በክልሉ ያለውን ጉዳይ ለመከታተል በተሰጡኝ ልዮ ተልእኮዎች ውስጥ ያረጋገጥኩት መሆኑን ግልፅ ለማድረግ እወዳለሁኝ።
ነገር ግን በግጭቶችና ጥቃቶች በእነዚህ የስድስት ወራት ጊዚያቶች በትግራይ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ዜጎች በታጠቂ ሀይሎች የተፈፀሙ ናቸው በተባሉ እርምጃዎች የበርካታ ንፁሀኖች ደም ፈስሰዋል ፣ዜጎች ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርገዋል ፣ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈፅመዋል፣ ሴቶችና ህፃናት ተደፍረዋል በቢሊዮን ብሮች የወጣባቸው የግልና የመንግስት የልማት ተቋማት ንብረቶች መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ የጤናና የትምህርት ተቋማትም ጭምር ወድመዋል ተዘርፈዋል ፣ተግዘው ተወስደዋል፣ የአርሶ አደሮች በሬ በጎች ፍየሎች እና የድሆች የእለት ምግብና የቤት መገልገያ ጥቃቅን ንብረቶችን ሳይቀር ጠፍተዋል ተዘርፈዋል።
በተለይ በእኔ እምነት በከፍተኛ የመንግስት ሀላፊነቶች ላይ እያለሁ ይህ እጅግ አሳዛኝ ጥፋት በህዝብ ላይ ሲደርስ ቀዳሚ የሚሆነው ጉዳቱን በሚቀንሱና ሌላ ተጨማሪ አደጋ በህዝቡ ላይ እንዳይደርስ በሚከላከሉ ህይወት አድን ስራዎች በፍጥነት በመሳተፍ መስራት ፣በአገር ደህንነት ላይ የተጋረጠውን ጉልህ አደጋ መቀልበስና አገሪቱን በአጠቃላይ ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ በሚጠቅሙ ተግባራት ላይ ማተኮር በዚህም በርካቶችን ከተጨማሪ ሞት እና የእጅግ የከፋ ጉዳት ለማዳን አቅም የተቻለውን ሁሉ ማድረግ መሆኑን ብገነዘብም ፤ ባለፋት ስድስት ወራት በነበሩ እጅግ ፈታኝና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ ሁኔታዎች በግሌ ለትግራይ ህዝብና ለመላው ያገራችን ህዝቦች በነበረኝ አገልግሎት ውስጥ በማናቸውም መልኩ ውሱንነቶች መኖራቸውን ባለመካድ መቆሜንና ህዝቡ ለዘላቂ ሰላሙ እና መረጋጋቱ አሁንም ቅድሚያ በመስጠት ከፊታችን ያለውን ወሳኝ የህይወት አድን ስራ ፣ ሰላም ግንባታና መልሶ ማቋቋም ተልእኮ በስኬታማነት እንድወጣ እንዲያግዘኝ በትህትና እማፀናለሁ።
በትግራይ የተከሰተውን ግጭት በማስቆም ሰብአዊ ቀውሰን የመግታት ጉዳይ ቀደም ሲል እንዳስቀመጥቁት የችግሮችን ስሪተ ነገርን መረዳትንና ሚዛናዊ አቋም መያዝን የሚጠይቅ፣ የችግሮቾን ተያያዥነትና ተፅእኖዎችን በጥንቃቄ መለየትን የሚሻ፣ እንዲሁም የመፍትሔ አሰጣጥንም በተመለከተ የሙሉ ስእል እይታን ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ፣ ለህይወት ማዳን ሰላምና መረጋጋት ቀዳሚ አጀንዳነት የተለየ ቁርጠኝነት የሚጠይቅ መሆኑን በሚገባ መረዳት ለዘላቂ መፍትሔ አሰጣጥ ውጤታማ አቀራረብ ሲሆን በዚህ ውስጥም የህዝብ ፍላጎትና ምልአተ ተሳትፎም አስኳል ጉዳይ መሆኑን መገንዘብን የሚጠይቅ ነው።
በአሁኑ ሰአት በትግራይ ክልል ቀደም ሲል በተከሰቱ ችግሮችና በየቦታዉ በሚያጋጥሙ ልዮ ልዮ ጥቃቶች ለዜጎች አስፈላጊውን መሰረታዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እና አስተማማኝ ፀጥታና ሰላምን ለማረጋገጥ በህዝብ ተሳትፎ ላይ የተለየ ስራ መስራትን የሚጠይቅ ሁኔታ መኖሩን መረዳት የሚያስፈልግ ነው። በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል የህዝቡን ፍላጎት የእለት ተእለት ችግሩንና ሁነኛ ስጋቱንም ጭምር በሚገባ በማድመጥ ሳይውል ሳያድር ለመፍታትና በሒደትም ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መሰረት የሚጥሉ አፋጣኝ ስራዎችን መስራት ላይ ትኩረት ማድረጉን በመልካም እድገትነት ሊሚወሰድ የሚገባ መሆኑን ሰላም ወዳድ ሀይሎችና በተለይም የሰላሙ ባለቤትና ዋና የሆነው የትግራይ ህዝብ በአስተውሎት እንዲገነዘቡት ያስፈልጋል።
በሌላው በኩል በግጭቶችና የፀጥታ መደፍረስ ጊዜ እነዚህ ጉዳቶች ተጠባቂ ናቸው የሚሉ የአጠቃላይ ድምዳሜዎች አዝማሚያና በወገኖች ላይ ለደረሱ አሳዛኝ ጉዳቶች የተለየ እና አስቸኳይ ትኩረት እንዳልተሰጠ የሚያስመሰሉ ክፍተቶች በፌደራል መንግስትና በጊዚያዊ አስተዳደሩ በተጨባጭ የተሰሩ ስራዎችን መና ለማድረግ ለሚሰሩ የውስጥና የውጭ የቅርብና የሩቅ ሴረኞች ምኞት ተጋላጭም የሚያደርጉ በመሆናቸው መለየትና መታረምም ይገባቸዋል።
በትግራይ በተከሰተው ችግር ላይ በግልፅ ወጥቶ ለመናገር እና ሁኔታውን በሚቀይር ስራ በመሳተፍ የመፍትሔው አካል የመሆን ጉዳይ የፖለቲካና የዘር ወገንተኝነትን አይጠይቅም። በመሆኑም ዜጎች በሁሉም ቦታ ለወገኖቻቸው እንዲደርሱ ከጥላቻ ንግግር ሰላባነት ወገኖቻቸውን በስራና በማህበራዊ አካባቢዎቻቸው በሙሉ እንዲጠብቁ በግልና በቡድን ጭምር ርህራሔና አቃፊነትን በመላበስ ለዜጎቻቸው የሰላም ወዳጅነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ልዝበት እንዲፈጠር አበክረው እንዲሰሩ በመደበኛና በሶሻል ሚዲያ ከሚቀነቀኑ ተንኳሽ ንግግሮችና በቅርብ የተለመዱ መጠሪያዎችን ከመጠቀም እንዲቆጥቡ ከዚህ የጠብ ገበያ ለማትረፍ ያሰፈሰፋ ሀይላትንም እንዲያሳፍሩ በአጠቃላይ ክልሉን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሰብአዊ ጥሪዬንም አቀርባለሁ ።
መላው የአገራችን ህዝቦች!
ሰላም የጀግኖች አጀንዳ ነው ! ብዙ መታገስን ፣ አስፈቶ ማሰብን ፣ ብዙ አይቻልሞችን መድፈርን ፣ ነገን ማየትንና በትላንት እውነታዎች ላይ ግልፅ መሆንንና መጨከንን የሚጠይቅ!
ከቅርብ ግዜ ወዲህ በወንድማማች ህዝቦች መካከል ውጥረትን ለመፍጠር ለአመታት የተሰሩ ስራዎችና በቸልተኝነትና በእልህ በተተው ጉዳዮች የሰውን ህይወት ማጥፋትና ከኖረበት ቀዬው ማፈናቀል የመሳሰሉ መራራ የጥላቻ ፍሬዎችን እየተመለከትን ቢሆንም ለአመታት ከተገነባው የአብሮነት እና የመተሳሰብ መልካም ዘመናት የጉዞ ታሪካችን ጋር የማይወዳደር በመሆኑ እንደ ህዝቦች ወደ ማስተዋል እና ስክነት ለመመለስ ሳንውል ሳናድር መስራት በመጀመር ለትውልዶች የምንሰንቀውን ስንቅ ከቂም ከጥላቻና ከበቀል ይልቅ መተማመን ፣ ይቅር
መባባል ፣ መደጋገፍንና አብሮነትን ለማጎልበት የሚበጁ መሆናቸውን የማረጋገጥ የትውልድ ሀላፊነት አለብን።
በዚህ አጋጣሚ በትግራይ ፀጥታና ሰላምን በማስፈን ፣ ፍትህን በማረጋገጥና ዘላቂ ሰላምን በማምጣት፣ ሰብአዊ እገዛ በማድረግና መልሶ ግንባታ ሒደት መላው የአገራችን ህዝቦች በተለይም የአጎራባች ክልሎችና የኤርትራ ህዝቦች፣ የፌደራል መንግስት ፣ የዲያስፖራ ኮሚዩኒቲ አባላት ፣ ምሁራን ፣ ባለሀብቶች ፣ የኮሚዮኒቲ ማእከሎች ፣ የሙያ ማህበራት ፣ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ተቋማትና ግለሰቦች ፣ የሚዲያ አካላት ማህበረሰብ አንቂዎች ፣ የሐይማኖት አባቶች ፣ የአገር ሽማግሌዎች ፣ የወጣት እና ሴቶች አደረጃጀቶች ፣ በግል አና በመንግስት ስራ የምትተዳደሩ ዜጎች ለዚህ አንገብጋቢ ተልእኮ ልባችሁን ግዜአችሁን ድጋፋችሁን እና አቅማችሁ የሚፈቅደውን ሁሉ በማድረግ እንድትሳተፋ የአደራ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
በመጨረሻም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይን ወቅታዊ ችግር በሁሉም መስክ በዘለቄታ ለመፍታት በሚያግዙ ገንቢና ሰላማዊ እንዲሁም ህጋዊ የአሰራርና የመፍትሔ አማራጮች ካላቸው አካላት ጋር በቅርበት ለመስራት ሙሉ በሙሉ ዝግጅት ያለው መሆኑን ስገልፅ በዚህ የታሪክ ሀላፊነት ወቅት ዜጎች የበኩላቸውን ለማድረግ እንዲረባረቡ የአደራ መልእክቴን በማስተላለፍ ጭምር ነው።
አብርሃም በላይ በርሀ የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግስት ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ
ግንቦት 2 ቀን 2013 ዓም