ምርጫ 2013

ማንኛዉም ገለልተኛ ታዛቢ የኢትዮጵያን ምርጫ ለመታዘብ በቅድሚያ የሃገሪቱን ሉዓላዊነት ሊያከብር እንደሚገባ ተገለፀ

By Tibebu Kebede

May 07, 2021

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ማንኛዉም ገለልተኛ ሃገር አቀፍ ወይም ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የኢትዮጵያን ምርጫ ለመታዘብ በቅድሚያ የሃገሪቱን ሉዓላዊነት ሊያከብሩ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለፀ፡፡

ምክር ቤቱ ጉዳዮን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ምርጫዉን የመታዘብ ጉዳይ የሃገሪቱን ህገ መንግስት ማዕቀፍ ከግምት ያስገባ መሆን አለበት ብሏል፡፡

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር ራሄል ባፌ ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን እንዲታዘብ መልካም ፈቃዷ ቢሆንም ህብረቱ አሁን ላይ የያዘውን አቋም በድጋሚ ሊያጤነው እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማይጻረር መልኩ ከታዛቢዎች ጋር ተነጋግሮ ምቹ ሁኔታን ሊፈጥር እንደሚገባ ያነሳው የምክር ቤቱ መግለጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲደረግ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን ላለመታዘብ የመወሰን ወይም አለመፈለግ መብቱን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንደሚያከብር በመግለጫው አብራርቷል፡፡

ምክር ቤቱ “ህብረቱ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ የይስሙላ ምርጫዎችን ሲታዘብ ኖሮ በዘንድሮው ምርጫ ከታዛቢነት ለመውጣት የወሰነበትን ምክንያትና ያልተግባባበትን ነጥብ ለባለ ጉዳዮ የኢትዮጵያ ህዝብ ማሳወቅ” እንዳለበትም ጠቁሟል ፡፡

በአወል አበራ