Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፊቼ ጫምባላላ በዓል በኮቪድ 19 ምክንያት በአደባባይ አይከበርም – አቶ ደስታ ሌዳሞ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተው የፊቼ ጫምባላላ በዓል ዘንድሮ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአደባባይ እንደማይከበር የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳደሩ የዘንድሮው የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ “ፊቼ ጫምባላላ” በዓል ከንክኪ በራቀ መልክ ሚያዝያ 29 እና 30 ቀን/2013 እንደሚከበር ነው የገለጹት፡፡

ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመርዳትና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባውም ርዕሰ መስተዳደሩ ዛሬ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ገልጸዋል።

የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ የሆነው ፊቼ ጫምባላላ” ከጥንት ጀምሮ ሲከበር የቆየ መሆኑን አስታውሰው፤ በዓሉ የተጣሉትን በማስታረቅ ፣ የተቸገሩትን በመርዳትና ለሰው ልጆችና እንስሳት ክብር በመስጠት የሚከበር ታላቅ በዓል መሆኑን አስረድተዋል።

ለበዓሉ ሲባል እንስሳት የማይታረዱበትና በቀያቸው በእንክብካቤ የሚያሳልፉበት እንዲሁም ዛፍ የማይቆረጥበት በመሆኑም እለቱን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በአሁን ወቅት በፍጥነት እየተዛመተና በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያሰከተለ ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ተዕዕኖ ምክንያት በዓሉ እንደወትሮው በአደባባይ በመሰባሰብ እንደማይከበርም ገልጸዋል።

ሆኖም በዓሉ ባህላዊ ትውፊቱን ሳይለቅ ዘንድሮ ሁሉም የብሄሩ ተወላጅ በየቤቱ ሆኖ የሚያከብረው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል።

ህብረተሰቡ የዘንድሮውን ፊቼ ጫምባላላ በአልን ሲያከብር እራሱን ከኮሮና ወረርሽኝ በመከላከል ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

በተለይ ከተጣላው ጋር ይቅር በመባባልና ከመዋደድ ባሻገር እርስ በእርስ በመደጋገፍ እንዲሆንም አቶ ደስታ መልእክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

Exit mobile version