Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመራጮች የምዝገባ ሒደት ባልተጀመረባቸው የምርጫ ክልሎች ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 13 ቀን ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የመራጮች ምዝገባ ሒደት ባልተጀመረባቸው የምርጫ ክልሎች ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ተወስኗል፡፡

ቦርዱ ከክልል መስተዳድር አካላት ጋር ባደረገው ከፍተኛ የትብብር ስራ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው የመራጮች ምዝገባ ባልተጀመረባቸው ቦታዎች የመራጮች ምዝገባን ለማስጀመር ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል፡፡

በዚህም ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በልዩ ሁኔታ እንዲከናወን ወስኗል፡፡

በዚህም መሰረት

• በምእራብ ወለጋ ዞን (ለቤጊ እና ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል ውጪ)
• በምስራቅ ወለጋ ዞን (ከአያና እና ገሊላ ምርጫ ክልል ውጪ)
• በቄለም ወለጋ ዞን
• በሆሮ ጉድሩ ዞን (ከአሊቦ፣ ጊዳም እና ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል ውጪ)
ከሚገኙት 31 ምርጫ ክልሎች መካከል በ24ቱ ላይ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በከማሽ ዞን ከሚገኙት አምስት የምርጫ ክልሎች በአራቱ የመራጮች ምዝገባ (ከሴዳል ምርጫ ክልል ውጪ) ከላይ በተጠቀሱት ቀናት እንዲከናወን ወስኗል።

ከዚህም በተጨማሪ የመራጮች ምዝገባ በጸጥታ ችግር የተነሳ ሳይከናወንበት የነበረው የአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን የሚገኙት ዳዋ ጨፌ፣ ጨፋ ሮቢት እና ባቲ ምርጫ ክልሎች በተመሳሳይ ሁኔታ የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 29 እስከ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ይከናወናል ተብሏል።

በመሆኑም ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያ እና ሲቪል ማህበራት የመራጮች ምዝገባን በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን መረጃን በመስጠት እና አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ በማድረግ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ ቦርዱ ጠይቋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version