የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገር ጠላቶችን ለማሸነፍ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሊቆሙ ይገባል – ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን

By Tibebu Kebede

May 03, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገር ጠላቶችን ለማሸነፍ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ጥሪ አቀረቡ።

ኢትዮጵያ ከ80 ዓመት በፊት ከገጠማት የውጪ ወረራ የሚመሳሰል ችግር እየገጠማት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት በመጪው ረቡዕ የሚከበረውን 80ኛ ዓመት የድል በዓል አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ ሰጥተዋል።

ዕለቱ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ አርበኞች እና የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በተገኘበት በአራት ኪሎ እንደሚከበር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ጠላቶቿ በዘርና በሀይማኖት ሊከፋፍሏት በመጣደፍ በኃይል ሊያስፈራሩ እየሞከሩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ጠላቶች ህዝቡና መሪዎች እንዳይተማመኑ ሴራ እየሰሩ መሆኑንም በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡

ሀያላን መንግስታት ሳይቀሩ ከግፈኞችና ከሀገር ጠላቶች ጎን ሲሆኑ የሀገር ውስጥ ባንዳዎችም ሀገር የማፍረስ ሴራው ደጋፊ ሲሆኑ ይታያልም ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ከውስጥም ከውጭም ጠላቶቿ ቢተባበሩባትም ሊያቆስሏት ይችሉ ይሆናል እንጅ አያሸንፏትም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በድል አድራጊነት ለህዝቦቿ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝብና በቅኝ አገዛዝ ስር ለነበሩ ሁሉ ተስፋና ኩራት ሆና ቀጥላለች ማለታቸውንም ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!