ኮሮናቫይረስ

በህንድ በአንድ ቀን ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች በኮቪድ ሲያዙ 3 ሺህ 689 ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል

By Abrham Fekede

May 02, 2021

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህንድ በአንድ ቀን ብቻ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች በትናትናው ዕለት በኮቪድ 19 ሲያዙ ዛሬ ደግሞ 3 ሺህ 689 ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡

ይህ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በሀገሪቱ ብዛት ያላቸው ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉበትና በቫይረሱ የተያዙበት ነው ተብሏል፡፡

ህንድ በትናትናው ዕለት 402 ሺህ እሁድ ደግሞ ከ392 ሺህ ሰዎች በላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡

ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት በየዕለቱ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሪንድራ ሞዲ በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር ከጤና ሚኒስትራቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡

ሖስፒታሎች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለመርዳት ትግል ላይ መሆናቸው ተነግሯል፡፡

ሆኖም የኦክስጅንና የአልጋ እጥረት ፈተና የሆነባቸው ሖሰፒታሎች በዋና ከተማዋ ደልሂ ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም በኦክስጅን እጥረት ምክንያት ሰዎች ለህልፈት እየተዳረጉባቸው ይገኛሉ ነው የተባለው፡፡

እስካሁን አሜሪካንን ጨምሮ 40 የሚደርሱ ሃገራት ለህንድ የኦክስጅንና የተለያዩ ድጋፎችን እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

ህንድ በአሁኑ ወቅት ከዓለም የክትባት አምራቾች የፊት ተርታ ላይ ብትሰለፍም በሀገር ውስጥ የክትባት አቅርቦት እጥረት እንደገጠማት ተሰምቷል፡፡

ይህንንም ተከትሎም የሀገር ውስጥ ፍላጎቷን ለማሳካት አስትራዜኒካ የተሰኘው ክትባት በጊዜያዊነት ወደ ውጪ እንዳይወጣ ውሳኔ አስተላልፋለች፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!