ቢዝነስ

ከእርድ የሚገኘውን ቆዳ በጥንቃቄ በማዘጋጀት በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ እንደሚገባ ተገለጸ

By Tibebu Kebede

May 01, 2021

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ለመጪዎቹ በዓላት ከሚፈጸም እርድ የሚገኘውን ቆዳ በጥንቃቄ በማዘጋጀት በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ እንደሚገባ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት አሳሰበ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ሽፈራው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ቀጣዮቹን የትንሳኤ እና የኢድ አልፈጥር በዓላት ምክንያት በማድረግ በሚከናወን እርድ ወቅት ማህበረሰቡ ለቆዳ ጥራት ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ25 ሚሊየን በላይ እንስሳት ለእርድ ይቀርባሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ውስጥም 25 በመቶው ብቻ ለገበያ እንደሚቀርብ አንስተዋል።

ለዚህም በአቅራቢዎች እና ተረካቢዎች መካከል ያለው የገበያ ትስስር አነስተኛ መሆን እና የግንዛቤ እጥረት ዋነኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም ከቀጣዮቹ በዓላት ጀምሮ የቆዳ ፋብሪካዎች ከተጠቃሚዎች በቀጥታ ምርቱን መሰብሰብ እንዲችሉ መፈቀዱን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በየአካባቢው የቆዳ መሰብሰቢያ ማዕከላት መኖራቸውን የገለጹት አቶ ዳኛቸው፥ ህብረተሰቡ ቆዳዎችን በጥንቃቄ በማዘጋጀት በወቅቱ ለገዥዎች ማቅረብ አለባቸው ነው ያሉት።

ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እና የሥራ ዕድል ለማሳደግም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በመላኩ ገድፍ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!