አዲስ አበባ ፣ ጥር 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጎንደር ከተማ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡
መነሻቸውን ጋሞ ያደረጉት የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች “ከጋሞ እስከ ጎንደር” በሚል መሪ ቃል ከ1 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ የሰላም ጉዞ ካደረጉ በኋላ ዛሬ ረፋዱን ጎንደር ገብተዋል፡፡
የሰላም ተጓዦቹ ጎንደር ከተማ ሲገቡ በከተማው በነዋሪዎችና ለጥምቀት በዓል ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በከተማዋ በተገኙ እንግዶች በማርሽ ባንድ የታጀበ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
የጋሞ የሀገር ሽማግላች በእርጥብ ሳርና በባህል አልባሳት ደምቀው የምርቃት ስነ ስርዓትም አከናውነዋል፡፡
አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ከተማሪዎችና ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱም የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች ለተማሪዎች አባቶች ጠብቀው ያቆዩአትን ሃገር እንጠብቅ በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከዩኒቨርስቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በሶዶ ለማ