የሀገር ውስጥ ዜና

ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዋርያትን እግር ማጠቡ የሰው ልጆች ፍጹም ትህትና አገልጋይነት የሚማሩበት ነው – የሃይማኖት አባቶች

By Abrham Fekede

April 29, 2021

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ የሐዋርያትን እግር ማጠቡ የሰው ልጆች ፍጹም ትህትና አገልጋይነት የሚማሩበት ተግባር ነው ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

ጸሎት ሐሙስ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ዛሬ ታስቦ ውሏል።

በስነ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ ሊቀነ ጳጳሳት፣ ቆሞሳት፣ የሃይማኖት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ የሐዋርያትን እግር ዝቅ ብሎ በማጠብ ትህትናን ያስተማረበትን ምሳሌ ለማስታወስ የሕጽበተ እግር ስነ ስርዓቱ የኮቪድ-19 ወረርሽን መከላከል መርህ በማድረግ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከትንሳኤ በፊት ያለውን አንድ ሳምንት ሰሞነ ሕማማት (የሕማማት ሳምንት) በማለት ትዘክረዋለች።

በሕማማት ሳምንት ከሚታሰቡት ዕለቶች መካከል የዛሬዋ ቀን ጸሎተ ሐሙስ ናት።

ጸሎተ ሐሙስ ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ የተወሓደ አምላክ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይበት ያደረበት በመሆኑ የተሰጠው ስያሜ መሆኑ የሃይማኖቱ አስተምህሮት ያስረዳል።

በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በጸሎተ ሐሙስ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙ የሃይማኖት አባቶች ኢየሱስ ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ የሐዋርያትን እግር ዝቅ ብሎ በማጠብ የፈጸመው ተግባር ፍጹም ትህትናና አገልጋይነትን ያስተማረበት መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታና አምላክ ሆኖ ሳለ ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር ማጠቡ የሰው ልጆች በትህትናና በመተሳሰብ መኖር እንደሚገባቸው የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በተለይም አገርን የሚመሩ ባለስልጣናት ዝቅ በማለት የሚያስተዳደሩትን ሕዝብ ማዳመጥና መመልከት እንዳለባቸውም የሚያመላከት መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም ኢየሱስ ክርስቶስ ያሳየው አገልጋይነት ባለስልጣናትና ሃላፊዎች ስልጣን ሳይገድባቸው ሕዝባቸውን ማገልገል እንዳለባቸውም ነው የእምነቱ ተከታዮች የገለጹት።

ነገ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የስቅለት እንዲሁም የፊታችን እሁድ የትንሳኤ በዓል ይከበራል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!