አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላ ሀገሪቱ ህብረተሰቡ የፋሲካ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በድምቀት እንዲያከብር በቂ ዝግጅት መደረጉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የፋሲካ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በበዓሉ ወቅት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝቡን ከጎኑ አሰልፎ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በርካታ የፀጥታ ስራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማክሰም ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የህግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ እያካሄደ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዚህም የጁንታውን ርዝራዦች፣ የኦነግ ሸኔ አባላት እና በመተከል ዞን የመሸጉ ሽፍቶችን ከተደበቁበት ስፍራ ሙሉ በሙሉ አድኖ ለፍትህ ለማቅረብ ሌት ተቀን እየሰራ እንደሚገኝም አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ለማድረግ ፖሊስ በብቃትና በገለልተኝነት በማገልገል ላይ ነው ብለዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት ሰራዊቱ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ታላላቅ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጠበቅ ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች በጀግንነት እየታደጋት ነው።
ህብረተሰቡ በመላ ሀገሪቱ የሚከበረውን የፋሲካ በዓልን ያለምንም የጸጥታ ችግር በድምቀት እንዲያከብር ኮሚሽኑ በቂ ዝግጅት ያደረገና የፖሊስ አባላትም በወትሮ ዝግጁነት ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የጤናና የፍቅር እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!