አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምስራቅ አፍሪካ ተጠሪ ማርሴል አክፖቮን ጋር ተወያዩ፡፡
አቶ ደመቀ በውይይቱ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ረገድ በምታከናውናቸው ተግባራት ድርጅቱ የሚሰጠውን ድጋፍ አድንቀው ያለው መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ ኮሚሽን ጋር በጋራ ምርመራ ለማካሄድ መወሰኑን ኢትዮጵያ በአድናቆት ትመለከተዋለች ብለዋል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚከሰት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከማንኛውም አካል በላይ ኃላፊነት የሚሰማው መሆኑን ጠቅሰው፥ የምርመራ ውጤትን ተቀብሎ የድርጊቱ ፈፃሚዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
የተለያዩ አካላት ባልተረጋገጠ መረጃ በመመስረት በመንግስት ላይ ገንቢ ያልሆኑ ትችቶችን እየሰነዘሩ መሆኑን አስታውሰው፣ የምርመራው ውጤት በመሬት ያለውን ተጨባጭ እውነታ እንደሚያሳይም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሚያከናውናቸው ተግባራት ከበሬታ ያተረፈ ተቋም መሆኑን ገልጸው፣ ተቋሙ በማይካድራ እና አክሱም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ያከናወናቸውን የምርመራ ተግባራት በአብነት አንስተዋል።
በወቅቱ አቶ ደመቀ በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ሁኔታን እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ የድርድር ሂደትን በተመለከተ ለተጠሪው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ማርሴል አክፖቮን በበኩላቸው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት የስራ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ በኩል እየተደረገላቸው ለሚገኘው ትብብርና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አያይዘውም ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር በትግራይ የጋራ ምርመራ ማካሄድን ጨምሮ በሌሌችም ተዛማጅ ስራዎች መልካም የስራ ግንኙነት መኖሩን ጠቅሰው፣ ይህም ለስራቸው ስኬት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት በምታደርገው ጥረት ድርጅታቸው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ስራቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አቶ ደመቀ ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!