አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሰሞኑን በኢትዮጵያ ጉዳይ ያወጣው መግለጫ የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ብቻ እንዲካሄድ የጸና አቋም እንዳላትም ተናግረዋል።
የሚኒስቴሩ ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው ሰሞኑን የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ አንዳንድ አካላት በኢትዮጵያ ዙሪያ የነበራቸውን የተዛባ አመለካከት የቀየረ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለትግራይ ክልል የሚያደርገውን ሠብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።
ሰሞኑን ከመላው አውሮጳ የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን “ዲፌንድ ኢትዮጵያ” በሚል ቡድን ተደራጅተው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚነዛውን የሃሰት ወሬ ለመከላከል እንዲሁም የኢትዮጵያን ትክክለኛ አቋም ለመግለጽ እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እና የሱዳ ድንበርን በተመለከተም አሁንም ኢትዮጵያ በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።
አምባሳደር ዲና ለመጪው አገራዊ ምርጫ የአውሮፓ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ይልካል ተብሎ እንደሚጠበቅም አምባሳደሩ ተናግረዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም 593 ዜጎች ከጂዳ፣ 297 ከሪያድ እና 16 ደግሞ ከፑንትላንድ መመለሳቸውን ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ብቻ እንዲካሄድ ኢትዮጵያ የጸና አቋም እንዳላትም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በማብራሪያቸው አስታውቀዋል።
ግብጽና ሱዳን ድርድሩን ከአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለማውጣት የሚያደርጉት ሙከራ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም አክለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሰሞኑ መግለጫው መንግስት በትግራይ ክልል ለሚያደርገው የሠብዓዊ ድጋፍ እውቅና በመስጠት ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።
የፀጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ፖለቲካዊ ነጻነት፣ የግዛት እና ሃገራዊ አንድነት በፅኑ እንደሚያከብር ማረጋገጡም እንዲሁ ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!