Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የህወሓት ቡድን ከ6 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያነት እንዳይጠቀም ተደርጓል – ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድን ጥቃት ከፈጸመበት ወቅት አንስቶ ከ6 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያነት እንዳይጠቀም ማድረግ መቻሉን አስታወቀ፡፡

በተጨማሪም ከ97 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ በሕግ አግባብ የውርስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሚመለከተው አካል መተላለፉንም ነው የገለጸው፡፡

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጀነራል አቶ ዓለምአንተ አግደው እንደገለጹት ሕወሓት ሲቆጣጠራቸው በነበሩና ገንዘብና ንብረታቸውን ለሕገ-ወጥ አላማው ሊጠቀምባቸው ይችላል በሚል በተጠረጠሩ ድርጅቶች እንዲሁም በጦርነት በተሳተፉ የጦር መኮንኖችና ሌሎች ባለስልጣናት ላይ በተደረገ የሃብት ክትትልና ምርመራ ውጤታማ ሥራዎች ተመዝግበዋል፡፡

ገንዘቡ እንዳይሸሽ መከላከል የተቻለው ኢትዮጵያን ከድተው ከሕወሓት ጋር በመሰለፍ በጦርነት የተሳተፉ ዋና ዋና ተጠርጣሪዎች ገንዘብና ሃብት ላይ በተደረገ ክትትልና ማጣራት ሥራ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ይፋ አድርጓል፡፡

እንዲሁም በኤፈርት/ት.ም.ዕ.ት ሥር በሚተዳደሩ እና ተያያዥ የሆኑ የተለያዩ ድርጅቶች ላይ በተከናወነ የሀብት ክትትልና ምርመራ ሥራ ሌላኛው መሆኑን ጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ በሕወሃት ሕገ-ወጥ ቡድንና በዚህ ቡድን ስር በነበሩ አመራሮች ቀጥተኛ ቁጥጥር ይደረግባቸው በነበሩና ቡድኑ የድርጅቶችን ገንዘብ ለወንጀል መፈጸሚያ ሊያውል ይችል የነበሩ ሦስት ሲቪል ማህበራት ላይ በተደረገ የሃብት ክትትልና ምርመራ ሥራ መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡

ለውርስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሚመለከተው አካል ከተላለፈው ከ97 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጋር በተያያዘም ገንዘቡ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 99 (2) እና (3) መሰረት ዕዳውን ሸፍኖ የሚተርፍ የፓርቲው ገንዘብ ካለ ለሥነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲውል በምርመራ ከተሰባሰቡ ማስረጃዎች ጋር አባሪ በማድረግ መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም ለቦርዱ እንዲተላለፍ ተደርጓል ሲሉ ዳይሬክተር ጄኔራሉ አስታውሰዋል፡፡

በአጠቃላይም ሕገ-ወጡ የሕወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ማግስት ጀምሮ ቡድኑ ይቆጣጠራቸው የነበሩ ገንዘቦችና ሀብቶችን ለተጨማሪ ጥፋት እንዳይጠቀምና እንዳያሸሽ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ በፍጥነት መሰራቱን ነው ያስታወቁት፡፡

በዚህም የመከላከል ሥራውን ውጤታማ ማድረጉንና አሁንም ቀሪ ሥራዎችን  ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version