Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 138 ሄክታር መሬት ለአልሚዎች አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 138 ሄክታር መሬት ለአልሚዎች አስተላልፏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላትና ከባለሃብቶች ጋር እየተወያዩ ነው።

በውይይቱ በመዲናዋ ዓመታትን ያስቆጠሩ የመሬት ጥያቄዎችን ለመመለስና በዘርፉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ካለው እድገት ጋር ተያይዞ እየጨመረ የመጣውን የመሬት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት 138 ሄክታር ለልዩ ልዩ አገልግሎች እንዲውል ለአልሚዎች ማስተላለፉ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህገወጦች ተይዞ የነበረውን መሬት ወደ መሬት ባንክ በማስገባት ለረጅም ጊዜያት ጥያቄ ሲቀርብባቸው የነበሩ እና ለከተማዋ እድገት የሚያስፈልጉ ተቋማት እንዲኖራት ለማስቻል አልሚዎችን በግልጽ መስፈርት በመለየት በልዩ ሁኔታ መሬት እንዲሰጥ በካቢኔ መወሰኑን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል ።

በከተማ አስተዳደሩ ለልዩ ልዩ አገልግሎት እንዲውል የተሰጠውን መሬትም አልሚዎች በአፋጣኝ አልምተው ለተፈለገው አላማ ማዋል ይኖርባቸዋልም ብለዋል ።

የከተማ አስተዳደሩም በመሬት እና መሬት ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋለውን የመሬት ወረራ እና ሌሎች ብልሹ አሰራሮችና ማነቆዎችን በመፍታት በህገወጥ የተያዘውን መሬት ወደ መሬት ባንክ በማስገባት ፣ 430 በሚሆኑ አመራሮችና ሰራተኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ እንዲህም ዘርፉን በቴክኖሎጂ የማዘመን ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑንም አመልክተዋል።

ለልማት የሚውል መሬት የተሰጣቸው ተቋማት እና ልዩ ልዩ ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው ለዘመናት ታጥረው የነበሩ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ በማስገባት በግልጽ መስፈርት ለተቋማት እና ድርጅቶች እንዲተላለፍ መደረጉ ከተማ አስተዳደሩ ለግልጸኝነት ፣ለተጠያቂነት እና ለመልካም አስተዳደር መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል ።

የከተማ አስተዳደሩም በሰጣቸው መሬት ለተፈለገው ልማት እንዲውል በአፋጣኝ ወደ ስራ እንደሚገቡም የተቋማት እና ልዩ ልዩ ድርጅት ተወካዮች ቃል መግባታቸውን ከፕረስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version