አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ያደረጉት ጉብኝት ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሚመነጭና ለአፍሪካ ሀገራት በሚሰጥ ትኩረት የተከናወነ በመሆኑ ስኬታማ ስምምነት የተደረሰበት እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊኒ፣ ኣኳቶሪያል ጊኒ እና ደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በጉብኝታቸውም ከሃገራቱ ጋር በተለያዩ መስኮች የመግባቢያ ስምምነቶች መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
ቃል አቀባዩም በመግለጫቸው ፖለቲካዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በቱሪዝም መስክ ከሃገራቱ ጋር ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በደቡብ አፍሪካ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ መደረሱን ያነሱት ቃል አቀባዩ በመንግሥት ደረጃ ቃል ተገብቷልም ነው ያሉት።
በመግለጫው ለ33ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ፥ “ግጭትና ጦርነትን በማስቆም ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታን ማመቻቸት” በሚል መሪ ሀሳብ በያዝነው ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
ጉባኤው በአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታ፣ በህብረቱ ተቋማዊ ለውጥ ትግበራ እንዲሁም የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን በተመለከተ ይመክራልም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ።
የኢትዮ ጅቡቲ የጠረፍ አስተዳደሮች ኮሚቴ ስብሰባ በጅግጅጋ እየተካሄደ መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ፥ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ የሃገራቱን ህዝቦች ጤናማ የትብብር ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።
ውይይቱ የድንበር ደህንነት የጸጥታ አስከባሪ አካላትን ትብብር፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን መዋጋት፣ የሃገራቱን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ማሳለጥ፣ የድንበር ንግድ የጉምሩክ አገልግሎት እንዲሁም ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ዝውውርን መከላከል ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮ ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 50ኛ ኣመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓልን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ የሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ ትብብር ከፍ ማለቱን አስረድተዋል።
ዘንድሮ የግንኙነታቸው 50ኛ ዓመት ሲከበርም በቀጣይ ስኬታማ ትብብሮችን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ የተለያዩ ስነ ስርዓቶች ይካሄዳሉ ተብሏል።
ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ጋር በተያያዘም በሊባኖስ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር እስከ ጥር 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ 238 ዜጎች ወደ ሀገራቸው ይገባሉ ብለዋል።
በዓላዛር ታደለ