Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ብሄራዊ የገጠር መሬት አስተዳደር መረጃ ስርአት አያያዝ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብርና ሚኒስቴር ብሄራዊ የገጠር መሬት አስተዳደር መረጃ ስርአት አያያዝ ይፋ አደረገ።

አዲሱ የመሬት ይዞታ የመረጃ ስርአት አያያዝ ደረጃውን የጠበቀ፣ ዘመናዊና ስራን የሚያቀላጥፍ መሆኑን በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ሲሰራበት የቆየው የመሬት ይዞታ ባህላዊ፣ መረጃው በወረቀት ላይ ብቻ የሚቀመጥ፣ አቅጣጫን ብቻ የሚጠቁምና የሴቶችን የመሬት ባለቤትነት የማያሳይ ነበር ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም የመሬት ይዞታ መረጃን በጥራት ለማግኘት አስቸጋሪ እንደነበርም ተገልጿል።

አዲሱ ስርአት ዘመናዊ የቅየሳ ዘዴን በመጠቀም ካርታን፣ ማሳን እንዲሁም በይዞታው አካባቢ የሚገኙ ጠቋሚ ነገሮችን የሚያሳይ መሆኑም ነው የተነገረው።

በቀላሉ ሪፖርቶችን፣ ትንተናዎችን እንዲሁም ስለመሬት ምርታማነት ለማወቅና የግብር አከፋፈል ስርአትን ለማቀላጠፍ የሚረዳ ስርአት መሆኑ ተጠቁሟል።

በመሆኑም አዲሱን ስርአት በመጠቀም የሁሉንም ክልል ማሳዎች መቀየስ፣ መመዝገብ እንዲሁም ሰርተፍኬት መስጠት ስለሚገባ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋት ከንድፈ ሀሳብ ወደትግበራ መግባት ይገባቸዋልም ነው የተባለው።

ህብረተሰቡም ሆነ ሀገሪቱ መሬትን በአግባቡ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እንዲጎላ በሰፊው መሰራት አለበት መባሉን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version