አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሩሲያ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያቀረቧቸውን ዕጩ ሹመት አጸደቀ።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የህገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ካቢኔ መበተኑ ይታወሳል።
የካቢኔውን መበተን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ፑቲን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ያቀረቧቸው ዕጩ በሀገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት ድጋፍ ማግኘቱ ተገልጿል።
ብዙም የፖለቲካ ልምድ የላቸውም የተባሉት ሚሃይል ሚሹስቲን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል።
አዲሱ ተሿሚ ከ424ቱ የዱማው መቀመጫ የ383ቱን ድምጽ ይሁንታ አግኝተዋል።
ፑቲን ያቀረቡት የህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ሃሳብ ግን በበርካቶች ዘንድ በመልካም አልታየም።
የሃገሪቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ፑቲን ሩሲያን የግል ንብረታቸው አደረጓት በሚል ይኮንናሉ።
አዲሱ እቅዳቸውም ከአራት አመት በኋላ የሚያልቀውን የስልጣን ዘመናቸውን በህገ መንግስት ማሻሻያ ሰበብ በማራዘም ሩሲያን ብቻቸውን ለመምራት ያለመ ነው በሚል ተችተዋቸዋል።