የሀገር ውስጥ ዜና

በዓለም አቀፍ አቅራቢዎች በጨረታ ይፈፀም የነበረውን የስንዴ አቅርቦት ለመቀየር እየተሰራ ነው

By Tibebu Kebede

January 16, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር አገልግሎት ኤጀንሲ በዓለም አቀፍ አቅራቢዎች በጨረታ ይፈፀም የነበረውን የስንዴ አቅርቦት ለመቀየር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

የአቅርቦት ሂደቱን ለማፋጠን የመንግስት ለመንግስት ግብይትን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን፥ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፅዋዬ ሙሉነህ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

የግብይቱ ተግባራዊ መሆን ሀገሪቱ ላይ ከዚህ ቀደም በደላሎችና በነጋዴዎች ይደርስ የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በመታደግ፥ ከጨረታ ጋር ታያይዞ የሚጠፋውን ጊዜ እና የንብረት ብክነት ለመቆጣጠር ያስችላልም ነው ያሉት።

ይህን የግብይት ሂደት እውን ለማድረግ በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመራ ቡድን የተቋቋመ ሲሆን፥ ቡድኑ በዩክሬን፣ ሩሲያ እና አውስትራሊያ የስንዴ ጥራት፣ መጠን እና አይነትን በተመለከተ ምልከታ አድርጓል ብለዋል።

ዳይሬክተሯ አያይዘውም ለተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የታዘዘው ስንዴ ወደ ሃገር ውስጥ እየገባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውስጥ ለኢትዮጵያ ንግድ ስራ ኮርፖሬሽን 400 ሺህ ሜትሪክ ቶን፣ ለብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን 200 ሺህ ሜትሪክ ቶን፣ በግብርና ሚኒስቴር የሚገዛ 155 ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ በግዥ ሂደት ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።

ከዚህ ውስጥ ለኢትዮጵያ ንግድ ስራ ኮርፖሬሽን የታዘዘው ስንዴ የተወሰነው ወደ ሃገር ውስጥ እየገባ መሆኑንም አውስተዋል።

በተያያዘም ኤጀንሲው ከተወገዱ ተሽከርካሪዎች፣ የተቋማት የተለያዩ ንብረቶች እና ቁርጥራጭ ብረቶች 32 ሚሊየን 669 ሺህ 809 ብር ከ97 ሳንቲም ማግኘቱንም ገልጸዋል።

ኤጀንሲው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ምቹ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር እየዘረጋ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ፥ የውስጥ ችግሮችን የመለየት፣ አደጃጀትን የማዘመን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትብብርና ቅንጅት ማሳደግን ጨምሮ የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ስራ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከአመታዊ በጀቷ ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው እና ከሃገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት 15 በመቶውን ለግዥ እንደምታውል መረጃዎች ያመላክታሉ።

በሙሃመድ አሊ