አዲስ አበባ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ፥ የጥምቀት በዓልን አከባበር እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኮሚሽኑ በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ከፌደራል እና ኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ባለፉት 6 ወራት ባደረገው ግምገማ በከተማዋ ከፍተኛ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ፣ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መኖራቸውን በመለየት አጥፊዎችን ለህግ ማቅረቡንም አንስተዋል።
ከከተማዋ ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘም በርካታ ወንጀል መፈጸሙን ያነሱት ኮሚሽነሩ፥ በዚህም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት 60 ሺህ ካሬ ሜትር ወደ መሬት ባንክ ገቢ ሆኗል ነው ያሉት።
እንዲሁም 10 ሺህ በሸራ እና ፕላስቲክ የተሰሩ ቤቶችን በማፍረስ የህግ ማስከበር ስራ መከናወኑንም ገልጸዋል።
ከመኪና እና ሌሎች የዘረፋ ወንጀሎች ጋር በተያያዘም ፖሊስ ኮሚሽኑ በተያዘው ወር ብቻ 438 ወንጀሎች መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም 523 ተጠርጣሪዎችን በመለየት 396ቱን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ጠቅሰው፥ 127ቱን በቁጥጥር ስር ለመዋል እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በፍሬህይወት ሰፊው