አዲስ አበባ ፣ ጥር 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) ውስጥ በተለማማጅነት የገባው የ17 አመቱ ታዳጊ ከምድር በ1 ሺህ 300 የብርሃን አመታት የምትርቅ አዲስ ፕላኔት አግኝቷል።
ወልፍ ኩኪዬር የተባለው ይህ ተለማማጅ ታዳጊ ፕላኔቷን ወደ ናሳ በገባ በሶስተኛ ቀኑ ማግኘቱም ነው የተነገረው።
ታዳጊው በክረምቱ ወቅት ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ለሁለት ወራት በናሳ በሚተዳደረው የህዋ በረራ ማዕከል ውስጥ በተለማማጅነት ሰርቷል።
በወቅቱም የሰው ልጅ ከሚኖርበት ስርዓተ ፀጸሃይ ውጭ ያሉ ፕላኔቶችን እንቅስቃሴ በሚከታተል ቴሌስኮፕ ክፍል ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል።
ስራ ላይ በነበረበት ወቅትም ሁለት ኮከቦችን የምትዞር አዲስ ፕላኔት እየፈለገ እንደነበርም ታዳጊው ወልፍ ይናገራል።
ከሳተላይት ምስሎችን እየተከታተለ ባለበት ወቅትም የከዋክብቱን ደማቅነት የሚያደበዝዝና እንግዳ የሆነ ጥላ ነገር ማስተዋሉንም ገልጿል።
ወልፍ በተመለከተው እና የሁለቱን ከዋክብት ብሩህነት ቀይሯል የተባለው እንግዳ ነገር ላይ በተሰራው ትንተናም አዲስ ፕላኔት መሆኗ ተረጋግጧል።
አዲሷ ፕላኔት ከምድር 6 ነጥብ 9 እጥፍ የሚበልጥ ግዝፈት ያላትና በሁለት ከዋክብት ዙሪያ የምትሽከረከር ስለመሆኗም ነው የተገለጸው።
በታዳጊው የተገኘችው ፕላኔት ቲ ኦ አይ 1338 ቢ የሚል ስያሜንም አግኝታለች።
ፕላኔቷ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላትና ምናልባትም ለሰው መኖሪያነት የማታገለግል ልትሆን እንደምትችልም ታዳጊው ጠቅሷል።
በናሳ የነበረው የተለማማጅነት ጊዜ እጅግ ስኬታማ እንደነበርም ተናግሯል።
ታዳጊው አሁን ላይ ኒው ዮርክ ውስጥ ወደሚማርበት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመልሶ ትምህርቱን መከታተል ጀምሯል።
ምንጭ፦ ቢቢሲ