አዲስ አበባ ፣ ጥር 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ተወላጅ ምሁራን ውይይት በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እንዳሉት፥ ውይይቱ ለክልሉ ወቅታዊ ችግሮች የሰከነ ሀሳብና ተሻጋሪ መፍትሄዎችን ለማደራጀት ሚናው የላቀ ነው።
አሁን ዋልታ ረገጥነት በሰፍበት ወቅት ሀገርንም ሆነ ክልሉ በአንድነት ፀንቶ እንዲቆም የሊህቃኑ ምክረ ሀሳብ ጎልህ ነውም ብለዋል።
የምሁራን መድረኩ ምክንያታዊ አማራጮችን በመጠቆም የነገውን ተስፍ ማሳየትም ይጠበቃልም ነው ያሉት።
“የማንነት፣ የብሄር ማንነትና አደረጃጀት ተራክቦና ልዮነት” በሚል ርእስ በቀረበ ጥናታዊ ፅሁፍ በሀገሪቱ ባለፉት አመታት በነበሩ ቀውሶች እና ተግዳሮቶቻቸውን በመለየት ለዛሬ የሚሆኑ የመፍትሄ ምክረ ሀሳቦች ቀርበዋል።
በተዛቡ ትርክቶች የክልሉ ህዝቦችን ለመለያየት የተሰሩ ስራዎች ችግሮች ተብለው ቀርበዋል።
በመፍትሄነትም ከፉክክር ይልቅ በትብብር እና አብሮነት ህዝቦች መቆም እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።
ተሳታፊ ምሁራንም ከዚህ ቀደም ልዩነትን በሚያሰፉ ስራዎች ላይ ልሂቃኑም ሆነ አመራሩ ማተኮሩ አሁን ለሚታየው ችግር ምክንያት በመሆኑ በጋራ ለመቆም አንድነቱ ላይ በትኩረት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
መድረኩ ነገ የሚቀጥል ሲሆን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ምክረ ሀሳብ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል ።
ሀይለየሱስ መኮንን