አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዳማ የግብርና መሳሪያዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ለአርሶ አደሮች ያልተሰራጬ የእርሻ መሳሪያ ክምችት እንደሚገኙ ተገለፀ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዳማ የግብርና መሳሪያዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪ ምልከታ አድርጓል።
ማምረቻ ኢንዱስትሪው ለሰባት አመታት በዱቤ ሸጦ ያልሰበሰበው ገንዘብ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ መድረሱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባደረገው ምልከታ አረጋግጧል፡፡
በምልከታውም መሰብሰብ የሚገባቸው ሂሳቦች ወቅታቸውን ጠብቀው አለመሰብሰባቸው እና የእርሻ መሳሪያዎች ሃብት ክምችት ወደ ግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ አለመድረሱ አርሶ-አደሮች በቴክኖሎጂ ታግዞ ስራውን እንዳይሰራ እንዳደረገው ተነግሯል።
የግብርና መሳሪያዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪው ባጋጠሙት ችግሮች ቴክኖሎጂዎቹን ወደ አርሶ አደሮች ማድረስ ላይ ዝቅተኛ አፈፃፀም እንዳለው የመስክ ምልከታ ቡድን አስተባባሪ አቶ አያሌው አይዛ ጠቅሰው፤ ከውጭ ወደ ሃገር ከገቡ የቆዩና በቂ መለዋወጫ የሌላቸው የሚወገዱ ትራክተሮች እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
አስተባባሪው የማምረቻ ኢንዱስትሪው ያጋጠሙትን ችግሮች በፍጥነት ፈትቶ አርሶ-አደሮች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚጠበቅበት በመግለፅ ቋሚ ኮሚቴውም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግላቸው ጠቅሰዋል ፡፡
የኢንዱስትሪው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ድሪባ ሁንዴ በበኩላቸው፤ የእርሻ መሣሪያዎቹ ሲገዙ የሀገሪቷን ነባራዊ መልክዓ-ምድር ሁኔታ ጥናት ሳይደረግበት በመከናወኑ ቴክኖሎጅዎቹ ወደ አርሶ- አደሩ እንዳይሰራጬ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የተገዙት የትራክተር መለዋወጫዎች የጥራት ችግር ያለባቸውና ከትራክተሮች ቁጥር ጋር በአሃዝ ተመጣጣኝ አለመሆናቸውንም አቶ ድሪባ ተናግረዋል።
ችግሮቹን ከሚመለከተው አካል ጋር በመወያየት በመፍታት የአርሶ-አደሩን የቴክኖሎጅ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ማብራራታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!