ቴክ

የመረጃ መንታፊዎች ዋትሳፕን እንደ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ተገለጸ

By Meseret Demissu

April 09, 2021

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የመረጃ መንታፊዎች በቢሊየን የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ያሉትን ዋትሳፕ የማህበራዊ የትስስር ገጽ ለአጥፊ ተልዕኮ እየተጠቀሙበት መሆኑን የበይነ መረብ ደህንነት ምርት አቅራቢው ቼክ ፖይንት ኩባንያ ገለጸ፡፡

የበይነ መረብ ደህንነት ተመራማሪዎች አዲስ አጥፊ ሶፍትዌር ያገኙ ሲሆን÷ የመረጃ መንታፊዎች በተጠቁ የዋትሳፕ የመልዕክት መቀበያዎች ቫይረስ ለማሰራጨት እየተጠቀሙ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

እንደ ቼክ ፖይንት መረጃ አደገኛ የሆኑ መተግባሪያዎች በጉግል ፕሌይ ስቶር ውስጥ እንደሚገኙና ከእነዚህ አደገኛ መተግበሪያዎች መካከልም አንዱ ‘FlixOnline’ መሆኑን ተገልጿል፡፡

ይህ አደገኛ መተግበሪያ ሆን ተብሎ በዓለም ዙሪያ ላሉ የአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚዎች ባልተገባ መንገድ የመዝናኛ አማራጮችን እንደሚያቀርብ ቃል በመግባት የመረጃ ጥቃት ለማድረስ እንደተዘጋጀ መረጃው ጠቁሟል፡፡

በዚህ መተግበሪያ ላይም የመረጃ መንታፊዎቹ ትክክለኛ ለመምሰል የኔትፍሊክስን “Netflix” ሎጎ እንደሚጠቀሙ ቼክፖይንት ገልጿል፡፡

የዋትሳፕ ተጠቃሚዎችም መተግበሪያው ትክክለኛ መስሏቸው ወደ ስልካቸው ከጫኑ የዋትሳፕ አውቶማቲክ ምላሽ መስጫን ንቁ በማድረግ ተንኮል አዘል ሶፍትዌሩ በስልካቸው ላይ ፍቃድ እንዲያገኝ እንደሚያደርግም ተነግሯል፡፡

ፍቃዱ ከተገኘ በኋላም ወደ ተጠቃሚዎች የሚደርሱ መልዕክቶችን ሁሉ አውቶማቲክ መልስ እንደሚልክ ነው የታወቀው፡፡

በዚህም የመረጃ መንታፊዎች ወደ ግል አካውንት ለመግባት እና የክሬዲት ካርድ ዝርዝሮችን ለመመንተፍ እንደሚያስችላቸው ተነግሯል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አጥፊ ተልዕኮ ባላቸው ሶፍትዌሮች የሚፈጸሙ የበይነ መረብ ጥቃቶች አዳዲስ እና ፈጠራ የታከለባቸው መሆናቸውን የገለጹት የቼክ ፖይንት የሞባይል ደህንነት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቪራን ሀዙም ናቸው፡፡

በመሆኑም ተጠቃሚዎች በዋትሳፕ ወይም በሌሎች የመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች በኩል የሚያገኟቸውን ማውረጃዎችን ፣ አገናኞችን (link) ወይም አባሪዎችን (attachment) ከመክፈታቸው ወይም ከመጫናቸው በፊት  መጠንቀቅ እንደሚገባቸው ኃላፊው ማሳሰባቸውን ኢመደኤ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!