አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሦስት ሳምንታት የኮቪድ ናሙና ከሰጡ ሰዎች ውስጥ 45 በመቶዎቹ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገለጸ፡፡
የከተማው ጤና ቢሮ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው በድሬዳዋ አስተዳደር የኮቪድ19 ወርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን መመሪያ በማያከብሩ ላይ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ነው የተገለጸው፡፡
የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ በዚህ ሶስት ሳምንት ውስጥ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
በዚሁ ሶስት ሳምንት ውስጥ 15 ሰዎች በኮቪድ-19 ህይወታቸው ማለፉንም ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የሟቾቹ ቁጥር በኮቪድ ህክምና መስጫ ማዕከል ውስጥ ህይወታቸው ያለፈውን እንጂ በተለያዩ ተቋማትና ህክምና ሳያገኙ በቤታቸው የሚሞቱትን ቁጥር እንደማይጨምርም ነው የገለጹት፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ሰሞኑን ሰዎች እየሞቱ መሆኑንና ይህም ሳይመረመሩ በኮቪድ19 ምክንያት የሚሞቱ ወገኖች መኖራቸውን አመላካች ነው ብለዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች የመከላከያ መንገዶቹ የሆኑትን እጅን መታጠብ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ /ማስክ/ ማድረግና ርቀትን መጠበቅ እንደሚገባቸው መናገራቸውን ከጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!