Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ቤት ኤኒይ ከተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ያሉባቸውን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ቤት ኤኒይ ከተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱን በሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አማካሪ ወይዘሮ ዘቢደር ቦጋለ እና የቤትኤኒ ምክትል ፕሬዚዳንት ክርስቲ ግሊሰን ተፈራርመውታል።

ወይዘሮ ዘቢደር ቦጋለ ስምምነቱ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህፃናት ያሉባቸውን ውስብስብ ችግሮች መፍታት ያስችላል ብለዋል።

ሁለንተናዊ ጥቅምና ደህንነታቸውን ትርጉም ባለው ደረጃ ለማስጠበቅም የማህበረሰቡና የባለድርሻ አካላት የሰመረ ቅንጅትና ተግባራዊ ምላሽ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድርጅቱ በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻና በአደራ ቤተሰብ በርካታ ህፃናት ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙና ቤተሰብን መሰረት ያደረገ አገልግሎት እንዲስፋፋ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ገልጸዋል።

አያይዘውም ድርጅቱ ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን በመደገፍ ረገድ እያበረከተ ላለው ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ስምምነቱ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ወላጆቻቸውን ላጡና ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ህጻናት ከተቋም የሚሰጥን እንክብካቤ በማስቀረት፥ ህጻናት ጎዳና እንዳይወጡ የሚያስችል መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version