Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ባለፉት 3 ዓመታት የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት መሻሻል ታይቶበታል – ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ጥር 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 3 ዓመታት የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎት መሻሻል ማሳየቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአማራ ክልል ባለፉት ሶስት ዓመታት በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ/ ድጋፍ ሲካሔድ የቆየው የእናቶችና ህጻናት ጤና ማሻሻያ ፕሮጀክት ተገምግሟል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች የጤና ቡድን መሪ አቶ ዘነበ አካለ፥ ፕሮጀክቱ ከአማራ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች የሚገኙ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻሉን ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ከ120 ሚሊየን ዶላር በሚበልጥ በጀት በ396 ወረዳዎች በሚገኙ ጤና ተቋማት ያልተሟሉ ቁሳቁሶችን፣ የማቆያ ቦታዎችና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ መሰራቱን ኢዜአ ዘግቧል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ኢትዮጵያ የእናቶች እና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ያለሙ 4 መርሃ ግብሮች ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

መርሃ ግብሮቹ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ የአዳጊ ክልሎች የጤና ስርዓት፣ ለንጽህና መጠበቂያ የሚያገለግሉ የዋሽ ምርቶችና አገልግሎቶች ተደራሽነት ላይ እንዲሁም የክትትል ግምገማና ተልዕኮ ስርጸት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።

Exit mobile version