አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በደቡብ ክልል በሰገን ህዝቦች ዞን በከማሼ ወረዳ የእርስ በእርስ ግጭት በማስነሳት ለሁለት መከላከያ አባላት ሞት እና ከ14 ሚሊየን ብር በላይ ንብረት ውድመት ምክንያት ነው የተባለ ግለሰብ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።
የቅጣት ውሳኔውን የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርባ ምንጭና አካባቢው ተዘዋዋሪ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ነው የወሰነው።
በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት ተከሳሽ ገመቹ ጎንፌ የመንግስት ሰራተኛ ነው።
የፌደራል አቃቢ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሹ በታህሳስ 12 ቀን 2011 ዓ/ም ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ በሰገን ህዝቦች ዞን ደራሼ ወረዳ ጋቶ ቀበሌ ቀጠና 3 የአከባቢው ኗሪዎችን በቋንቋ በመከፋፈል ከደራሼ ወረዳ ጋር መቀጠል አይቻልም በማለት ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ፍርድ ቤት እነ ከበደ ገልገሎ በሚል መዝገብ በተመሳሳይ ወንጀል ከተከሰሱ 26 ሰዎች ጋር በጋራ በመሆን በዜጎች መካከል የእርስ በእርስ ግጭት አሰነስቷል ሲል በክሱ አመላክቷል።
የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አዋጅ ቁጥር 414/96 አንቀጽ 32/1 ለ እና አንቀጽ 36/1 እንዲሁም 240/2 ን በመተላለፍ በተከሰሰበት የእርስ በእርስ ግጭት ማስነሳት ወንጀል በወቅቱ በጸጥታ ማስከበር ስራ ላይ የነበሩ ሁለት የመከላከያ አባላት ህይወት በማጥፋት ከ14 ሚሊየን 787 ሺህ ብር በላይ ንብረት እንዲወድም እና እንዲዘረፍ በማድረግ እንዲሁም በርካታ ዜጎች ከመኖሪያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉ በክሱ ተጠቅሷል።
በተከሳሹ ላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃ የተመለከተው ፍርድቤቱ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን የተሰጠ ቢሆንም በተገቢው መከላከል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ተጥሎበታል።
በዛሬው ዕለት በዋለው ችሎት በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
በታሪክ አዱኛ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!