Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኢትዮ-ቴሌኮም በሰሜን ምዕራብ ሪጅን የአራተኛ ትውልድ (4ጂ) የኢንተርኔት አገልግሎት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ምዕራብ ሪጅን የአራተኛ ትውልድ (4ጂ) ኤል.ቲ.ኢ የኢንተርኔት አገልግሎት አስጀምሯል።

አገልግሎት የጀመረባቸው ከተሞች ባሕር ዳርን ጨምሮ ፍኖተሰላም፣ ዳንግላ፣ እንጅባራ፣ ቡሬ፣ ደብረማርቆስ እና ቻግኒ ናቸው።

የጀመረው የኢንተርኔት አገልግሎት በቀጠናው የነበረውን የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት በ14 እጥፍ ያሻሽለዋል ነው የተባለው።

በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከሥፍራው በቀላሉ ለማስተዋወቅ፣ የንግድ ሥርዓቱን ለማሳለጥ፣ ለኢንቨስትመንት፣ የትምህርት ተቋማትን አሠራር ቀላል ለማድረግና ለሌሎች አገልግሎቶች መልካም አጋጣሚ ነውም ተብሏል።

በመርኃግብሩ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወርቀሰሙ ማሞ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝን ጨምሮ የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ሠራተኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ግዙፍ ከሚባሉ ተቋማት አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ተመራጭ ብቻ ሳይሆን አንደኛ እንዲሆን እየሠራ እንደሆነም ተናግረዋል።

127 ዓመታት ያስቆጠረው ኢትዮ ቴሌኮም በበርካታ ለውጦች ውስጥ አልፏል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለዜጎቿ የቴሌኮም አገልግሎት የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗንም አንስተዋል።

በሦስት ዓመት የዕቅድ ትግበራ ውስጥ ከሚያከናውናቸው ተግባራት የአራተኛ ትውልድ አገልግሎት መስጠት አንደኛው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በ2020 የተጀመረውን የአምስተኛው ትውልድ(5ጂ) የኢንተርኔት አገልግሎት በኢትዮጵያ በ2022 ለማስጀመር እየተሠራ እንደሚገኝ አብመድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version