Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል – አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢሲ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆንም የምርጫ ፀጥታ ክልላዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

ክልሉ ለምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አቶ ኦርዲን ገልፀዋል።

ምርጫ 2013 ለማካሄድ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረገ ሲሆን የመራጮች ምዝገባም ተጀምሯል።

በሀረሪ ክልልም ከ2 መቶ በላይ በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች መራጮች ለምርጫ የሚያስፈልጋቸውን ካርድ መውሰድ ጀምረዋል።

በሀረሪ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አዲሱ በቀለ እና ሌሎች ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለምርጫው ያደረጉትን ዝግጅት ነግረውናል።

በምርጫው ተሳትፎ ላይ የእያንዳንዱ መራጭ ድምፅ ዋጋ አለው ብለዋል።

የሀረረ ከተማ ነዋሪዎችም የምርጫ ተሳትፎው ዋጋ መኖሩን በማወቅ ህብረተሰቡ መሳተፍ እንዳለበት ተናግረው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም ሁሉም የበኩሉን መወጣት ይኖርበታልም ይላሉ።

ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ከማሟላት በተጨማሪ ሰላማዊ ፣ነፃ እና ፍትሀዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሰፊ ሰራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አቶ ኦድሪን ነግረውናል።  ከቅድመ እስከ ድህረ ምርጫ ድረስም ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ የምርጫ ፀጥታ ኮሚቴ ተቋቁሟል።

ኮሚቴው ወደ ስራ መግባቱን የነገሩን ርዕሰ መስተዳድሩ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የፀጥታ ችግሮችም ተለይተዋል ነው ያሉት።

ከፌዴራል አካላተ ጋር በቅንጅት የሚሰራው ኮሚቴ ችግሮቹን ከመለየት ባለፈ ስጋቶቹን ለማክሸፍ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችንም ቀድሞ አዘጋጅቷል።

እነዚህን ስራዎች ሁሉ ቀድሞ እየሰራ የሚገኘው ኮሚቴ ከህብረተሰቡ እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋርም በጋራ እየሰራ ነው ብለዋል።

የምርጫ ፀጥታ ኮሚቴው ከመከላከያ፣ከፌዴራል፣ ከክልሉ ፖሊስ ጋር ነው በጋራ እየሰራ የሚገኘው።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ ምርጫውን ሰላማዊ ለማድረግ የሁሉም ህብረተሰብ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ሚና የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ  በምርጫው  በስፋት ለመሳተፍም አሁን እየተከወነ ባለው የመራጮች ምዝገባ  በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

በዙፋን ካሳሁን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

Exit mobile version