አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2013 (ኤፍቢሲ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና አትሌቶች ማህበር የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያካሄደውን ምርጫ ተቃወሙ፡፡
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የአትሌቶች ማህበር ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያካሄደውን ምርጫ በመቃወም የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በዚህም ኦሎምፒክ ኮሚቴው ያካሄደው ህገ ወጥ ምርጫ ነው ብሏል፡፡
ምርጫው የአትሌቲክስ ስፖርትን የሚጎዳ መሆኑን ጠቅሰው የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሀገሪቱን ከውድድር እንዳያግዳት ስጋት አለን ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት የተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሙሉ ዝርዝር፡-
በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ግቢ ውስጥ ድንኳን በመትከል የተደረገውን ህገወጥ ምርጫ በሚመለከት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ በኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር፣ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ አሰልጣኞች ማህበር የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫና የፌዴሬሽኑ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር መግለጫ፣
- የኦሎምፒክ ኮሚቴም ሆነ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች የሚመሩበትን መመሪያ ካለም አቀፍ የስፖርት ማህበራት ዋና ዋና የህግ ምሰሶዎችን በመውሰድ በዋናነት በሃገሪቱ መንግስት በተወከለ የስፖርት ኮሚሽን ከሚያወጣው የስፖርት ማህበራት መመሪያ በመነሳት መሆን ሲገባው መንግስት ሆነ ስፖርት ኮሚሽን አያገባውም በሚል ንቀትና ከአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ህግና ደንብ የሚቃረኑ የህግ አንቀፆችን በመጨመር የተፈፀመ ሲሆን በአንድ ሃገር ውስጥ ያሉ የስፖርት ማህበራት ከሃገሪቱ የልማት ስትራቴጂና ፖሊስ በመነሳት ተጨባጭ ሁኔታዎችን በሚቃኝ መንገድ መሆን ሲገባው የፌደራል ስፖርት ምክር ቤት የሰጠውን አቀጣጫ ወደ ጎን በመተው የተከናወነ ምርጫ በመሆኑ ተገቢ አለመሆኑን እንገልፃለን ይንንም የሃገራችን መንግስት ጉዳዩን በማጣራት አስፈላጊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፤
- ታህሳስ 25/2013 ዓ.ም. በሃዋሳ በተካሄደው 45ኛ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ጠቅላላ ጉባኤ ስለ ቀጣይ ምርጫ በኦሎምፒክ ኮሚቴው ፕሬዝዳንት ሞሽን ቀርቦ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ሃሰብ በመስጠት ምርጫ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ 2020 በኋላ እንዲሆንና ያለው ስራ አስፈፃሚ እስከ መስከረም 2014 ዓ.ም. ድረስ እንዲቀጥል በሙሉ ድምፅ ውሳኔ ካገኘ በኋላ ምርጫ ማካሄዱ ተገቢነትና ህጋዊነት የለውም እንላለን፤
- አንድ የስፖርት ማህበር (የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ) ጉባዔ ማካሄድ የሚችለው በዓመት አንድ ጊዜ ወይም አስቸኳይ ጉዳይ ሲያጋጥም አንድ አስቸኳይ ጉባዔ ማካሄድ ሲኖርበት ተደጋጋሚ ጉባዓዎችን በማካሄድ የአትሌትንና የህዝብን ገንዘብና የስፖርት ትጥቅ በከፍተኛ ደረጃ ለብክነት የዳረገ በመሆኑ በሚመከተው የመንግስት አካል ሊመረመር ይገባዋል እንላለን፤
- ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የቅርጫት ኳስ ፕሬዝዳንትነታቸው በጠቅላላ ጉባዔ ምርጫ ያልተከናወነና ያልፀደቀ በመሆኑ ለኦሎምፒክ ኮሚቴ ለፕሬዝዳንትነት በእጩነት ቀርበው ሊመረጡ ስለማይችሉና ህጋዊነት የሌለው በመሆኑ እንደገና በሚመለከተው አካል ሊፈተሸ ይገባዋል፤
- በህገወጥ ምርጫው ላይ ከተመረጡ ስራ አስፈፃሚዎች መካከል የክብደት ማንሳት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆኑት የስፖርት ማህበራት የሚፈቅደውን አገልግሎት ዘመናቸው ስምንት ዓመት ያለፈ በመሆኑ የተመረጡበት አግባብ ህገወጥ በመሆኑ ሊሰረዝ ይገባዋል፤
- የሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴና የአትሌት ብርሃኔ አደሬ በኦሎምፒክ ኮሚቴ ከፍተኛ አመራርነት መግባታቸው ካደረጉት የሃገርን ሰንደቅ ዓላማ ማስከበር አንፃር ተገቢ ቢሆንም ሊወክላቸው የሚገባው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ አንጋፋ አትሌቶች ማህበር ወይም ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ አትሌቶች ማህበር የተወከሉ ባለመሆናቸው ህጋዊ መስመሩን ያልተከተለ ነው፤
- አንድ ሃገራዊ የስፖርት ማህበራት ምርጫ መካሄድ ያለበት በግልፅና የሚዲያ አካላት ባሉበት መሆን ሲገባው በድብቅ በኦሎምፒክ ኮሚቴ ግቢ ውስጥ በተተከለ ድንኳን መካሄዱ ግልፅነት የጎደለውና ከጥቅማ ጥቅም ጋር የተያያዘ ስለሚያስመስለው እና ህጋዊ መሰረት ስለሌለው የሚመለከተው የሃገራችን መንግስትና ስፖርት ኮሚሽን መርምሮት ምርጫው እንዲሰረዝ ለዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ደብዳቤ እንዲፅፍ እንጠይቃለን፡፡
በአጠቃላይ አሁን ባለው የኦሎምፒክ ኮሚቴው አሠራርና አደረጃጀት የምናስበውና የምንጠብቀውን የቶኪዮ 2020 ጨዋታ የሚያደብዝዝና የአትሌቶቻችንን ስነ-ልቦና በመጉዳት ውጤት እንዲበላሽ ስለሚያደርግና ያለን ግንኙነት ከአለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የሚላኩ የተለያዩ ሰርኰላሮችና ፌዴሬሽኑ የሚልካቸው የምዝገባና ሌሎች መሠል ደብዳቤዎች እየደረሱ ባለመሆኑ በገለልተኛ ኮሚቴ የኦሎምፒክ ኮሚቴው እንዲመራና የአገራችን የኦሎምፒክ ወጤት እንዲቀጥል በጋራ አንጠይቃለን፡፡
ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አቋም መግለጫ በመቀጠል ከኢትዮጵያ አትሌቲክ አትሌቶች ማህበር የተሰጠ የአቋም መግለጫ፣
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!